የሰላምና የአብሮነት እሴትነቱ የጎላው የኣሪ ብሄር ዘመን መለወጫ በአልን የዓለም ቅርስ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ባህልና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ

የሰላምና የአብሮነት እሴትነቱ የጎላው የኣሪ ብሄር ዘመን መለወጫ በአልን የዓለም ቅርስ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ባህልና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ

የ2018 ዓ.ም የኣሪ ብሔር ዘመን መለወጫ የዲሽታ ግና በዓል የማርበርግ ወረርሽኝ ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ በጂንካ ሁለገብ ስታዲየም በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች ተከብሯል።

የ2018 ዓ.ም የኣሪ ብሄር ዘመን መለወጫ በአካባቢው የተከሰተውን የማርበርግ ወረርሽኝን ተከትሎ ፕሮቶኮሉን ለመጠበቅ ሲባል ከወትሮው በተለየ መልኩ ጥቂት ተሳታፊዎች በተገኙበት ነው በጅንካ ሁለገብ ስታዲየም የተከበረው።

በአባቶች ባህላዊ ምርቃትና መልካም ምኞት ስነ-ስርዓት በተጀመረው የበአሉ አከባበር ላይ ንግግር ያደረጉት የኣሪ ዞን ባህልና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ጋልሺ፤ ላለፉት አስርት አመታት የኣሪን ብሄር ባህል ለማስተዋወቅ ሰፊ ስራ ሲራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ዘንድሮ በተሻለ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ቢደረግም የማርበርግ ወረርሽኝ ክስተት በተፈለገው ልክ እንዳይከበር ማድረጉን ገልጸው፤ በውስን ሰዎች በጥንቃቄ እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።

የበአሉ መከበር ለማህበረሰቡ ሰፊ አበርክቶ እንዳለው በመጥቀስ በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ይሰራልም ብለዋል።

የኣሪ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው፤ በአሉ ከዚህ ቀደም በሁሉም መዋቅሮች በስፋት ሲከበር መቆየቱን አንስተው እሴቶቹ ለማህበራዊ እድገት ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የተከሰተው ወረርሽኝ በአሉ በተናጠል እንዲከበር ማስገደዱን ያነሱት አስተዳዳሪው፤ ሁሉም በዚሁ መልክ ሊያከብር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአሉን በአለምአቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ የተጀመሩ ጥረቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ይህንኑ ከዳር ለማድረስ ይሰራልም ብለዋል።

በአሉ ሲከበር የወረርሽኙን የመከላከያ ፕሮቶኮሎች መሰረት አድርጎ እየተከበረ ሲሆን በዚህ ረገድም የጤና መዋቅሩ ሚና የሚያስመሰግነው ስለመሆኑም አስረድተዋል።

በክብር እንግድነት የተገኙት የክልሉ ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኦላዶ ኦሎ፤ ባህልና ቱሪዝም ለህብረ ብሄራዊት አንድነት በሚል መሪ ቃል በድምቀት ለማክበር የታለመ ሲሆን በዓሉ በጥቂቱም ቢሆን መልካም እሴቶቹን የምንካፈልበት አኩሪ ፌስቲቫል ጭምር ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ይህንን አኩሪ ባህል ወደ ትውልድ ለማሸጋገር በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ እንደሚሰራ በመጠቆም ለማህበረሰቡ እሴት መልማት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ዘጋቢ: ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን