የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” በዓለም ቅርስነት በመመዝገቡ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈ
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” በዓለም ቅርስነት በመመዝገቡ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
የሚኒስቴሩ የእንኳን ደስ አላችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል።
ከኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ፤
ሀገራችን ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ስሟን የሚያስጠሩ ክብሯን ከፍ የሚያደርጉ ድንቅ የሆኑ ባህላዊ እና ኪናዊ ፀጋዎች ባለቤት ነች፡፡ ከባህላዊ ፀጋዎቿ መካከል ህዝባዊና ሀይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ በዓላትና ባህላዊ እሴቶቻቸው የማህበረሰቡን አብሮነትና መስተጋብር በማጠናከር የህዝብ ለህዝብ ትስስርና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ያላቸው ሚና አይተኬ ነው፡፡
የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ሀገራት የባህል እሴቶችንና ትሩፋቶችን በመጠቀም፣ የባህል ተቋማትን በማላቅ እና የባህል መገለጫዎቻቸውን በማስፋትና በመጠቀም ትውልድንና ሀገርን ገንብተዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያም ይህንኑ ዘርፍ በማልማት የባህል እሴቶቻችንን፣ ሀገር በቀል እውቀቶችን እና የባህል ተቋማትን እንዲጠኑ፣ እንዲሰነዱ፣ እንዲለሙ፣ እንዲጠበቁ እና ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፋ የባህል ልማት ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች ትገኛለች፡፡
የዚሁ የባህል እሴት ልማት ሥራ አካል የሆነው የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” በዓለም ቅርስነት በመመዝገቡ እንኳን ደስ አለን፤ እንኳን ደስ አላችሁ! እያልን “ጊፋታ” በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት መመዝገቡ በዓሉ ባህላዊ ዕሴቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ እንዲሁም ለሀገራችን የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
“ጊፋታ” በወላይታ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ በዓል ሲሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የሕዝቡ የማንነት መገለጫ የሆነ የአሮጌው ዓመት ማብቂያና የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ በዓል ነው፡፡
በድጋሚ እንኳን ደስ አለን፤ እንኳን ደስ አላችሁ!
የኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

More Stories
3ኛው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የክለቦች ሻምፒዮና የምድብ ድልድል ይፋ ሆነ
በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት መስጠትና ተግቶ በመስራት ከድህነት መውጣት ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
ኢትዮጵያን ለዘመናት ከቆየችበት ቁስል ለማላቀቅ ባለፉት የለውጥ አመታት በርካታ ፖለቲካዊ ተግባራት ማከናወኑን መቻሉ ተገለጸ