ሀዋሳ፡ ታህሳስ 01/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቡርጂ ዞን ጤና መምሪያ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻን በተመለከተ ለጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።
በስልጠናው የመክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በቡርጂ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኡሜ ቸኮል፥ ስልጠናው ቀጣይ ለምንሠራቸው ሥራዎች አቅም የሚፈጥር በመሆኑ በአግባቡ እንዲከታተሉ አሳስበዋል።
ከታህሳስ 03-06/2018 ዓ.ም ድረስ ቤት ለቤት በሚደረግ ጉብኝት እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት እንደሚሰጥ የቡርጂ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ላኦ ኮኖ ገልጸዋል።
ዘመቻው በዞኑ በሁሉም ቀበሌያት እንደሚሰጥ የገለጹት አቶ ላኦ ከአስራ ሰባት ሺህ በላይ ህጻናትን ለመከተብ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ከዘመቻው ጎን ለጎን በምግብ ዕጥረት የተጎዱ ህጻናት ልየታ፣ የፊስቱላ ልየታ፣ የማርበርግ ቅኝት እና አሰሳ ህክምናዎች እንደሚደረጉ ኃላፊው ጠቁመዋል።
በቡርጂ ዞን ጤና መምሪያ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ወንድሙ ሰለሞን በበኩላቸው፣ ስለ ፖሊዮ ክትባት ጠቀሜታ ግንዛቤ የመፍጠር እና ህብረተሰቡን የማንቃት ሥራ እንደሚሠራ አንስተዋል።
የፖሊዮ ቫይረስ ራሱን እየቀያየረ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ያነሱት አቶ ወንድሙ ያንን ለመከላከል በዚህኛው ዙር የሚሰጠው ክትባት ከወትሮው እንደሚለይ ገልጸዋል።
4ኛ ዙር የክትባት ዘመቻው ከታህሳስ 03-06/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ዘጋቢ: አሀዱ አሸናፊ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የጎፋና ኦይዳ ህዝቦች የባህል፣ የታሪክና የቋንቋ ሲምፖዚየም በሳውላ ከተማ እየተካሄደ ነው
ጥራት ያለው ቡና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ
የግብርና ቴክኖሎጂን በማስፋት አርሶ አደሩ ለገበያ የሚተርፍ ምርት እያመረተ መሆኑ ተገለጸ