የደረሱ ሰብሎችን የቤተሰብ ጉልበትና የልማት ቡድን አደረጃጀት በመጠቀም በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የባዳ ቀበሌ አርሶ አደሮች ተናገሩ
በልዩ ወረዳው በመኸር ሰብሎች ከተሸፈነው 8 ሺ 7 መቶ 81 ሄክታር ማሳ እስካሁን ባለው ሂደት ከ7 ሺ 1 መቶ 49 ሄክታር በላይ ማሳ መሰብሰቡን የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ገልጿል።
አርሶ አደር አስናቀች አኖሬ እና ታደሰ አሾሬ በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ባዳ ቀበሌ የመሀል ባዳ ጎጥ አርሶ አደሮች ሲሆኑ በአካባቢው የደረሱ የባቄላ፣ ስንዴና ገብስ ሰብሎችን የቤተሰብ ጉልበት ተጠቅመው በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አተርና ባቄላ ወቅተው ቤት ማስገባታቸውን የተናገሩት አርሶ አደሮቹ፤ አሁን ላይ የደረሱ የስንዴና ገብስ ሰብሎችን የማጨድና የመሰብሰብ ሂደት ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ምርታማነቱም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ እንደሆነም አመላክተዋል።
ወጣት አርሶ አደር ተከተል አማኑኤል፣ ማሞ ብርሃኑ እና ሙላቱ ግንታሞ በልማት ቡድን ተደራጅተው የደረሱ የደጋ ሰብሎችን እያሰባሰቡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በምርት አሰባሰቡ የመረዳዳትና የመተጋገዝ እሴት የሆነውን የደቦ የስራ ባህል ተጠቅመው ለአረጋውያንና አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
በልዩ ወረዳው በ2017/18 ምርት ዘመን በመኸር እርሻ ከተሸፈነው 8 ሺ 7 መቶ 81 ሄክታር ማሳ እስካሁን ባለው ሂደት 7 ሺ 149 ነጥብ 9 ሄክታር ማሳ መሰብሰቡን የገለጹት የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መብራቱ አበራ ናቸው።
በሂደቱ 92 በመቶ የሚሆነው የደረሱ ሰብሎች መሰብሰባቸውን የተናገሩት አቶ መብራቱ ከዚህም 3 ሺ 7 መቶ 97 ነጥብ 95 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
ምርታማነቱ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በአንፃራዊነት የተሻለ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ለዚህም የአርሶ አደሩ የግብዓት አጠቃቀም መሻሻልና NPS ማዳበሪያ በDAP ማዳበሪያ ተቀይሮ በመጠቀም የተገኘ እምርታ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ባለሙያውና ደጋፊ አመራሩ የተጠናከረ የድጋፍና ክትትል ስራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
ዘጋቢ: ጡሚሶ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በመጽናቴ ያገኘሁት ውጤት ነው – አርሶ አደር ደፋር ታደመ
20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሰላም መጠናቀቁ ተገለፀ
የተከሰተውን ማርበርግ ቫይረስ በተቀናጀ መልኩ ፈጣን ግምገማና ምላሽ በመስጠት ለመቆጣጠር ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል – አቶ እንዳሻው ሽብሩ