በመጽናቴ ያገኘሁት ውጤት ነው – አርሶ አደር ደፋር ታደመ

‎በመጽናቴ ያገኘሁት ውጤት ነው – አርሶ አደር ደፋር ታደመ

በመጽናቴ ያገኘሁት ውጤት ነው ሲሉ በኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ የጃሎ ቀበሌ አርሶ አደር ደፋር ታደመ ገለጹ፡፡

‎አርሶ አደር ደፋር ታደመ ይባላሉ። በኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ የጃሎ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ለእናት ሀገር ዋጋ የከፈሉ የአስር አለቃነት ማዕረግ ያላቸውና አገልግሎታቸውን ጨርሰው አሁን ላይ የመንግስት ጡረተኛ ናቸው።

‎አርሶ አደር ደፋር በጡረታ ከሥራ ሲሰናበቱ ምርጫቸውን ወደ ቤት መግባትና መጦርን አላደረጉም። ይልቁንስ በግብርናው ልማት ዘርፍ ሌላ ታሪክ ማስመዝገብና ለሌሎች መትረፍን እንጂ።

‎አርሶ አደሩ እንደሚናገሩት ከውትድርና ቤት ከወጡ በኋላ ወደ አካባቢው ሲመለሱ ሊለማ የማይችል ደረቅ መሬት የገጠማቸው ሲሆን ተስፋ ባለመቁረጥ ወደ ልማት ገቡ።

‎ወታደር ለዓላማው ጽኑ በመሆኑ እጅ ባለመስጠት የነበረውን የውሃ አማራጭ መጠቀምና በጽናት በማልማት ራዕያቸውን ማሳካትን ምርጫቸው አደረጉ።

‎ሌላኛው ፈተናቸው የነበረው በአካባቢው የነበረው የጸጥታ ችግር ሲሆን ለሠላም ዘብ ከመቆም በተጨማሪ ከማሳቸው አልተለዩም። ይህ ደግሞ ለልማት ያላቸውን ጽኑ አቋም ያሳዩበት መሆኑን በማሳቸው የተገኙ ሁሉ የሚመሠክሩት ነው።

‎በርካቶች አበረታቷቸው፤ በሙያቸውም ደገፉና አሁን ላይ የጽናታቸውን ፍሬ ከመመገብ በተጨማሪ መቁረስ ጀምረዋል።

‎አርሶ አደሩ ትኩረታቸውን ባደረጉበት የሙዝ ምርት ለምግብነት ከሚያስፈልጋቸው አልፈው አምርተው ለገበያ በማቅረብ ወደ ሀብት እየቀየሩት ነው።

‎በአንድ ዙር ከ40 እስከ 60 ሺህ ብር መሽጥ የሚችሉበት አቅም ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሩ፤ በዓመት እስከ 200 ሺህ ብር ገቢ ሊያገኙ እንደሚችሉ አመላክተዋል።

‎ለዚህ ነው በኮሬ ዞን የሶስተኛ ዙር ሰልጣኝ አመራሮች ተግባራዊ ስልጠናና ተሞክሯቸውን ለመካፈል በማሳቸው የታደሙት።

‎በዚህ ጊዜ አርሶ አደሩ ማሳቸውን ብለው ለመጡ አመራሮች በአቅራቢያቸው ያለውን ውሃ ለመጠቀምና በሰፊው ለማምረት የውሃ መሳቢያ እና በቂ መኖ በመኖሩ ዝርያቸው የተሻሻሉ ላሞች እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

‎የኮሬ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስታረቀኝ አንደባ፤ ሞዴል አርሶ አደር ደፋር በብዙ ችግሮች መካከል ያሳዩት ጽናትና ልማት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ምርቱ እንዲሰፋ ቀድሞ ከሚደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ከጎናቸው እንደሚቆሙ አመላክተዋል።

‎ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን