20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሰላም መጠናቀቁ ተገለፀ

20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሰላም መጠናቀቁ ተገለፀ

ሀዋሳ: ሕዳር 29/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በፌደሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት በሆሳዕና ከተማ የተከበረዉ 20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሰላም መጠናቀቁን የበዓሉ የፀጥታ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

የበዓሉን መጠናቀቅ ተከትሎ የፀጥታ ግብረ-ኃይሉ የፀጥታ ስራዎችን ተግባር ገምግሟል፡፡

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከማድረግ ባለፈ ህዳር 27/2018 ዓ.ም ደማቅ የጎዳና ላይ ትርዒት ማቅረባቸውን የተናገሩት የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ተመስገን ካሳ፥ ለበዓሉ በሰላም መጠናቀቅ ከመጀመሪያዉ ጀምሮ በተደራጀ ዕቅድ ላይ የተሰራዉ ስራ ነዉ ብለዋል፡፡

የፌደራልና የክልል ፀጥታ መዋቅር እንዲሁም የክልሉ አመራሮች፡ የኦሮሚያ ክልል ላደረጉት አስተዋጽኦ ኃላፊዉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ህዝቡ በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ላሳየዉ ፍፁም ጨዋነትና ለቃሉ በመታመኑ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው፥ የታዩ ዉስንነቶችም ቢሆን ለቀጣይ ትምህርት ይወሰድባቸዋል ብለዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሁለት ዓመት አስደናቂ ስራ ሰርቶ ማየታቸዉን የተናገሩት የደቡብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ደስታ ተመስገን፥ ሁሉም የፀጥታ መዋቅር በመቀናጀቱ በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ህብረተሰቡ በዓሉ የራሴ ነዉ ብሎ ያደረገዉ ተግባር ትልቅ ክብርና ምስጋና ሚገባዉ ነዉ ብለዋል፡፡

ለበዓሉ ስኬታማነት የፀጥታ ኃይሉ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መስራቱን የገለፁት የማዕከላዊ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀኔራል አብድሮ ከድር፥ ህብረተሰቡ ለበዓሉ እና መሪዉ ያሳየዉ ተግባር ምስጋና የሚገባዉ ነዉ ብለዋል፡፡

ሁለቱ ዕዞች በጋራ በደረጉት ስምሪት የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በሰላም ወደ አዲስ አበባ መግባታቸዉንም ተናግረዋል፡፡

ህዝቡ በዓሉን ለመታደም ካለዉ ፍላጎት አንፃር በነቅስ መዉጣትና የማክበሪያ ቦታ ጥበት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝብ ወደ ስታዲየም መግባት ያለመቻል መኖሩን የጠቀሱት የግብረ ኋይሉ አባላት ያም ሆኖ ህብረተሰቡ የፀጥታ መዋቅሩን ትዕዛዝ በመቀበልና በመተባበር ያደረገዉ ተግባር ምስጋና የሚገባዉ እንደሆነ ልፀዋል፡፡

የሀገር መከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስ ከክልሉ ፀጥታ ጋር የነበራቸዉ መቀናጀት ለበዓሉ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረዉም ጠቅሰዋል፡፡

በበዓሉ ማክበሪያ ቦታ በስርቆት ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን የፀጥታ መዋቅሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር በመያዝና ወደ ህግ በማቅረብ ወዲያዉኑ ዉሳኔ እንዲያገኙ በማድረግ ማረሚያ መግባታቸዉንም የግብረኅይሉ አባላት ገልፀዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የህብረተሰቡ ተሳትፎና ትብብር ከፍተኛ ምስጋና የሚገባዉ ነዉ ብለዋል፡፡

ዘጋቢ: ድልነሳው ታደሰ