የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን እንዲከበር ሲወሰን ዓላማው ብሔር ብሔረሰቦች ባህሎቻቸውን በመለዋወጥ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር ሃገራዊ መግባባትን እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው – የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር
ሀዋሳ፣ ህዳር 28/2019 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን እንዲከበር ሲወሰን ዓላማው ብሔር ብሔረሰቦች ባህሎቻቸውን በመለዋወጥ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር ሃገራዊ መግባባትን እንዲፈጥሩ ማድረግ መሆኑን የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በኢፌዴሪ ፌደሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት” በሚል መርህ ቃል እየተከበረ ያለዉ በዓል አንዱ አካል የሆነዉ የሲምፖዚየምና የምክክር ቀን መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ ወደ አብሮነትና የሠላም ተምሳሌት ወደሆነችዉ ሆሳዕና ከተማ በሠላም መጣችሁ ብለዋል።
በዓሉ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎለብትና ህብረ ብሄራዊነትን የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል ።
ዘንድሮ ለ20 ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስከበር የሚያስችሉ መደላደሎችን የሚንፈጥርበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የዘንድሮ በዓል የመላው ጥቁር ህዝቦች የላብ እና የደም ውጤት የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተመረቀበትና አዳዲስ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ወቅት የሚከበር መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገውም ጠቁመዋል።
የበዓሉ መከበር የሀገር መንግስት ግንባታ ጉዞን የሚያፋጥንና ዲሞክራሲያዊ ህብረ ብሄራዊነትን የሚያጠናክር እንደሆነም ወ /ሮ ፋጤ ገልጸዋል ።
በህዝቦች መካከል ሰላምና መቻቻል እንዲመጣ በማድረግ ረገድም በዓሉ ትልቅ ሚና ያለው እንደሆነ ጠቁመዋል።
በዓሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተለያዩ ቱባ ባህሎቻቸውን ለዓለም የሚያሳዩበት መድረክ እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን እንዲከበር ሲወሰን ዓላማው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቱባ ባህሎቻቸውን በመለዋወጥ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር ሃገራዊ መግባባትን እንዲፈጥሩ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል ።
ባለፉት ጊዜያት ለ19 ጊዜ የተከበሩ በአላትም ህዝቦች ወንድማማችነትን አጠናክረው እንዲሄዱ ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዘንድሮ በዓል በታላላቅ ሀገራዊ ድሎች የታጀበ በዓል ነዉ ያሉት ዋና አፈጉባኤው ዳግማዊ አድዋ የሆነው የታላቁ የህዳሴ ግድብ የተመረቀበት እና ሌሎች አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ወቅት የሚከበር እንደሆነ ገልጸዋል።
ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያ ህዝቦችም የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጀምሮ መጨረስን አሳይቷል ያሉት ዋና አፈ ጉባኤው የክልሉ መንግስትም ከፍተኛ ጥረት በማድረጉ ሊደነቅ እንደሚገባ ጠቅሰዋል ።
ዘጋቢ:- ተሻለ ከበደ

More Stories
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አባል በመሆናቸው ከድንገተኛ ህክምና ወጪ መዳን እንዳስቻላቸው ተገልጋዮች ገለጹ
ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የኢሠራ ባሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መሠረተ ድንጋይ አስቀምጧል
3ኛው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የክለቦች ሻምፒዮና የምድብ ድልድል ይፋ ሆነ