የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ለ20ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገለጹ

ሀዋሳ: ሕዳር 26/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀገር አቀፍ ደረጃ‎ ለ 20ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

“ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው 20ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን፥ ህዳር 29 በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡

አስተያየታቸውን ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሰጡ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች፥ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበሩ፥ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ከማጠናከር ባለፈ፥ የሀገሪቱን ብዝሃ ባህል፣ ቋንቋና ወግ እንዲሁም እሴት ለማስተዋወቅ ይረዳል ብለዋል።

በሆሳዕና ከተማ የሊችአምባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ወልደአማኑኤል ሀሬቦ በሰጡት አስተያየት፥ የዘንድሮ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሆሳዕና ከተማ መከበሩ እንዳስደሰታቸው ጠቁመው፥ ከተማቸው እንደዚህ አይነት እጅግ ትልቅና ሀገራዊ በዓል ለማዘጋጀት በመብቃቷ የፈጠረባቸው ስሜት ልዩ መሆኑን ገልፀዋል።

ከመላው ሀገሪቱ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ እንደ ቤታቸው ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን የገለፁት አቶ ወልዴ፥ አብዛኛው የከተማው ነዋሪ እለቱን በጉጉት እየጠበቀው መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በሆሳዕና ከተማ የሴችዱና ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደስታ ፎርሲዶ፥ ከተማችን የምታስተናግደው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ኢትዮጵያን በአንድነት በሆሳዕና ከተማ ላይ የምናይበት ምቹ አጋጣሚ ነው ብለዋል። ለዚህም እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን በመጠቆም።

ወጣት ማርታ ካሣ በበኩሏ በሰጠችው አስተያየት ወጣቶች ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ የህዝባቸውን ነባር እሴት ለማወቅ እድል የፈጠረ አጋጣሚ መሆኑን ገልፃ፥ በዕለቱም ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ እንደምታሳልፍ ተናግራለች።

በሆሳዕና ከተማ የወዜ ስታር ሆቴል ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ወልደአማኑኤል አብዮ በበኩላቸው፥ በዓሉን አስመልክቶ የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልፀው፥ በሆሳዕና ከተማ ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ ከመንግስት የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር በቅርበት ሲሰራ እንደነበር ጠቁመው፥ እንግዶችን በተሟላ መስተንግዶ ተቀብሎ ለመሸኘት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

ለ20ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሆሳዕና ከተማ መከበሩ በከተማው የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ያስቻለ መሆኑን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ በክልሉ ያሉ ጸጋዎችን ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አመላክተዋል።

20ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ህዳር 29 ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡

ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ