የነገ ሀገር ተረካቢ በሆኑ ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና ጉልበት ብዝበዛን በመከላከል ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ሊሰራ እንደሚገባ ተመላከተ

የነገ ሀገር ተረካቢ በሆኑ ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና ጉልበት ብዝበዛን በመከላከል ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ሊሰራ እንደሚገባ ተመላከተ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የነገ ሀገር ተረካቢ በሆኑ ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና ጉልበት ብዝበዛን በመከላከል፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ለሀገር ጠቃሚ ትውልድ እንዲሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነቱን በተገቢ እንዲወጣ በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የህፃናት ፓርላማ አባላት ጠያቁ።

የልዩ ወረዳው ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽ/ቤት በበኩሉ በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቀረት እንዲቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስተውቀዋል።

በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የህፃናት ፓርላማ ፕሬዝዳንት ህፃን ሠላማዊት ወ/የሱስ እና ምክትል ፕሬዝዳንት እሴይ ተክሌ በሰጡት አስተያየት የነገ ሀገር ተረካቢ በሆኑ ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና የጉልበት ብዝበዛን በመከላከል ለራሳቸውና ለሀገር ጠቃሚ ትውልድ እንዲሆኑ ለማስቻል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ወላጆች የልጆቻቸው ቀጣይ ህይወት እንዲሰምር በጊዜያዊ ጥቅም በመከተል ለጥቃትና ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ እንዲሆኑ ከማድረግ በአግባቡ በማሳደግና በማስተማር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ያስፈልገል ብለዋል።

እንደ ህፃናት ፓርላማ አበላት በልጆች ዘንድ የሚስተዋለውን የግንዛቤ ችግር መቅረፍ እንዲቻል በተላያዩ ጊዜያት በት/ቤቶች በድራማ መልክ አስተማሪ የሆኑ ነገሮችን በማዘጋጀት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ኢንስፔክተር እዮብ ዴልባሞ እና ወ/ሮ በላይነሽ ተሰማ በሰጡት አስተያየት ወላጆች በግንዛቤ እጥረት ጊዜያዊ ጥቅምን ብቻ በማሰብ ልጆቻቸው ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ ከአቅም በላይ የሆነ ሥራ እንዲሰሩ ለተለያየ ጥቃትና ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ እንዲሆኑ የማድረግ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል።

በልጆች ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና የጉልበት ብዝበዛን በማስቀረት በእንክብካቤ በማሳደግ እንዲሁም በማስተማር ለራሳቸውና ለሀገር ጠቃሚ ትውልድ እንዲሆኑ ለማስቻል ከወላጆች ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ሁላችንም ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

በሙዱላ ከተማ 03 ቀበሌ የህፃናትን ደህንነት ማስጠበቅ ሥራ ከሚስሩ አካላት መካከል ወ/ሮ እታላማ ዱጉኖ በሰጡት አስተያየት በቀበሌው በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ከተቋቋመው ቡድን ጋር በመሆን በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ሴቶቾና ህፃናት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ደሳለች ማቴዎስ በበኩላቸው እንደ ልዩ ወረዳው በህፃናት ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ጥቃቶችንና የጉልበት ብዝበዛን ለመከላከል በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሥራዎች በተቀናጀ ሁኔታ እየተሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በልዩ ወረዳው በሉ በሁሉም ቀበሌያት እና በከተማ አስተዳደሩ በህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አስወጋጅ ኮሚቴዎችን በመቋቋም ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቀረት ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዘርፉ በተሠራው የግንዘቤ ሥራ ከህብረተሰቡ በደርሰን ጥቆማ መሠረት ጥቃት ባደረሱ አካላት ላይ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ሃላፊዋ ጠቁመዋል ።

ቤተሰብ ልጆችን በተገቢው ተንከባክቦ በማሳደግና በማስተማር የተሻለ ደረጃ በማድረስ የወላጅነት ግዴታውን መወጣት እንዳለባቸዉ በመገንዘብ ለጊዜያዊ ጥቅም ብሎ ለጉልበት ብዝበዛና ለተለያየ ጥቃት ከመዳረግ መቆጠብ ያስፈልጋል ሲሉ አሳሰበዋል።

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የህፃናትን መብትና ደህንነት በማስጠበቅ የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመከላከል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በመደገፍ ውጤታማ ለማድረግ የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል ።

ዘጋቢ: ሙሉነሽ ለማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን