በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ወጣቶች የሚደረገው የስልጠና እና የግብዓት ድጋፍ ለሥራቸው ውጤታማነት እያገዛቸው መሆኑን ተናገሩ

በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ወጣቶች የሚደረገው የስልጠና እና የግብዓት ድጋፍ ለሥራቸው ውጤታማነት እያገዛቸው መሆኑን ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኬሌ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጁ በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ወጣቶች የሚደረገው የስልጠናና ግብዓት ድጋፍ ለሥራቸው ውጤታማነት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ተናገሩ።

‎የኬሌ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ የሚያደረገው የስልጠናና ግብዓት ድጋፎች ለሥራቸው ውጤታማነት እያገዛቸው መሆኑን በኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ወጣቶች ገልጸዋል።

‎የርሆቦት እንጨትና ብረታብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ዳንኤል ዳሪሙ ኮሌጁ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን በቀላሉ መሥራት እንዲችሉ በብረታብረት ብየዳና በሌሎች ዘርፎች ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

‎የይሳኮር እንጨትና ብረታብረት ሥራ ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ ወጣት ቸርነት ክፍሌ በበኩሉ የእንጨት መሥሪያ ማሽን በአነስተኛ ዋጋ ሠርቶ እየተጠቀሙ መሆናቸውን ገልጾ፥ ከኮሌጁ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግሯል።

‎ከኮሌጁ አንዳንድ ማሽኖችን በውሰት ተጠቅመው ሥራቸውን እየሠሩ እንደሚመልሱም ወጣት ቸርነት አስታውቋል።

‎ኢንተርፕራይዞቹ እንደሚናገሩት ከኮሌጁ የሚደረገው የስልጠናና ግብዓት ድጋፎች ለሥራቸው ውጤታማነት እያገዛቸው ነው።

‎ኮሌጁ ለሚያደርገው ድጋፍ ያመሰገኑት ወጣቶቹ፥ እነዚህንና መሰል ድጋፎችን በማጠናከር የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያደርጉትን ጥረት ማገዙን እንዲቀጥል አሳስበዋል።

‎አቶ ደግፌ አየለ የኬሌ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ምክትል ዲንና የቴክኖሎጂ ሽግግር ኤክስቴንሽን ሥራ ሂደት አስተባባሪ፥ ኮሌጁ በርካታ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን የመሥራት አቅም ያለው መሆኑን ጠቁመው፥ ለኢንተርፕራይዞች ባሸጋገሩት ስልጠናዎችና ቴክኖሎጂዎች ጥሩ ውጤት ማየታቸውን አመላክተዋል።

‎የኬሌ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ ሰማልኝ አብርሃም፣ ኮሌጁ ለኢንተርፕራይዞችና ለአካባቢው ማህበረሰብ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የክህሎት ክፍተት ላይ እንዲሁም የሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

‎ኮሌጁ 50 በመቶ ሰልጣኞቹን የማሰልጠንና 50 በመቶ ደግሞ ለኢንተርፕራይዞች ድጋፍ የመስጠት ሥራ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

‎ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን