የማርበርግ ቫይረስ የመከላከልና ቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ ገለፁ
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በጂንካ ከተማ ተገኝተው የቫይረሱን የመከላከል ሥራ የተመለከቱ ሲሆን ለህክምና አጋዥ የሚሆኑ ግብዓቶችንም ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ድጋፍ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በዚህን ወቅት እንደገለፁት፤ በአሁን ወቅት የቫይረሱ ስርጭትን ለመቆጣጠር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ከጤና ሚኒስቴርና ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት እየሠራ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
በተዋረድ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስተዳድር እና ጤና ቢሮ እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ሥራው እየተመራ መሆኑንም ዶ/ር መልካሙ ተናግረዋል።
የተደረጉ ድጋፎችም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት የተደረጉ ሲሆኑ በሽታውን ለመቆጣጠር መረጃዎችን ዲጂታላይዝድ አድርጎ ለማሳለጥ አጋዥ የሆኑ ግብዓቶች ስለመሆናቸውም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
ሁሉም ሰው ከባለሙያዎች የሚተላለፉ የመከላከያ መንገዶችን በመጠቀም የበሽታው ስርጭት ይበልጥ ሳይስፋፋ መቆጣጠር እንዲቻል የበኩሉን እንዲወጣም ዶ/ር መልካሙ ጠይቀዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በበኩላቸው፤ በአሁን ወቅት በቫይረሱ የተጠረጠሩ አካላት ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ገልፀው የመከላከል ተግባሩ ቀን ከሌት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይ የመከላከል ሥራውን አጠናክሮ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ትኩረት ተደርጓል ሲሉም አቶ እንዳሻው ተናግረዋል።
ከጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል በሽታው ከተከሰተ ወዲህ መሰል ድጋፎች ተደርገው የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ተጠናክሮ አገልግሎቱን እንዲሰጥ አቅም መፍጠሩን የገለፁት አቶ እንዳሻው፤ በዕለቱ ስለተደረገው ድጋፍም በክልሉ ጤና ቢሮ ስም አመስግነዋል።
ሕዝቡ ራሱን ከበሽታው ለመከላከል የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲያደርጉም አቶ እንዳሻው አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ወጣቶች የሚደረገው የስልጠና እና የግብዓት ድጋፍ ለሥራቸው ውጤታማነት እያገዛቸው መሆኑን ተናገሩ
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በእንሰት ዘር ብዜት ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ህዳር 18/2018 ዓ.ም #ደሬቴድ – ቀጥታ ስርጭት #ዜና24 #ዜና #ደቡብቴቪ