የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በእንሰት ዘር ብዜት ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በእንሰት ዘር ብዜት ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን በጌዴኦ ዞን የራጴ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።
በወረዳው ሁሉም ቀበሌዎች እንሰት አብቃይ መሆናቸውንና የእንሰት ፉንታ(ሀምቾ) ቆረጣ ሥራ መጀመሩን የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊና የዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ኢያሱ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡
በአንድ ጀምበር የተለዩ ከ61 ሺህ በላይ ፉንታዎች መቆረጣቸውን የጠቆሙት አቶ ኢያሱ፥ በአጠቃላይ ከሚቆረጡ ከ168ሺህ ፉንታዎች ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ የእንሰት ችግኝ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡
ከእንሰት ችግኝ ብዜት ሥራ ጎን ለጎን የአመራረት ዘይቤን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የአርሶ አደሩን የምግብ ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የምርታማ አከባቢዎችን ተሞክሮ የማስፋፋት ሥራ በትኩረት እየተተገበሩ መሆናቸውን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ምክትል እና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ደያሶ አስታውቀዋል፡፡
በአንድ ጀምበር የሀምቾ ቆረጣ መረሐ-ግብር ላይ አግኝተን ካነጋገርናቸው የወረዳው አርሶ አደሮች መካከል ገብሬ ሆርዶፋ፣ ብርሃኑ በራሶና ሌሎችም በቂ የእንሰት ችግኞችን በማዘጋጀት ከራሳቸው አልፎ ለገበያ በማቅረብ የገቢ አማራጫቸውን ለማስፋት ተግተው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዞኑ አንዳንድ አከባቢዎች እንሰት ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለምግብነት እየደረሰ መሆኑን በተጨባጭ ማየታቸውን የጠቆሙት አርሶ አደሮቹ ቀደም ሲል በአከባቢው አንድ እንሰት ለምግብነት የሚደርሰው ከአምስት ዓመት በኋላ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ይህም ረጅም ዓመት ቆይታ በምርታማነታቸው ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ መሆኑን የገለጹት አርሶ አደሮቹ የተሻሉ ተሞክሮዎችን በመተግበርና የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የተዘረጉ ስትራቴጂዎችን በመከተል ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
ዘጋቢ: ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በእንሰት ዘር ብዜት ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ

More Stories
በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ወጣቶች የሚደረገው የስልጠና እና የግብዓት ድጋፍ ለሥራቸው ውጤታማነት እያገዛቸው መሆኑን ተናገሩ
የማርበርግ ቫይረስ የመከላከልና ቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ ገለፁ
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ህዳር 18/2018 ዓ.ም #ደሬቴድ – ቀጥታ ስርጭት #ዜና24 #ዜና #ደቡብቴቪ