ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በብዝሃነታቸው ውስጥ ሀገራዊ አንድነታቸውን አጠናክረው በሚያስቀጥሉ ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወልቂጤ ክላስተር አመራሮችና ሰራተኞች ”ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብር ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል 20ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በወልቂጤ ከተማ አክብረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የህዝቦችን የእርስ በእርስ ትስስርን በማጠናከር በብዝኃነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ስር እንዲሰድ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
የዘንድሮው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተመረቀበት፣ ከተስፋ ወደ ሚጨበጠው ብርሀን በተሸጋገርንበት አመት የሚከበር መሆኑን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በዚህም ህዝቦች በብዝሃነታቸው ውስጥ ሀገራዊ አንድነታቸውን አጠናክረው በሚያስቀጥሉ ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
አክለውም የበዓሉ መከበር ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና ወንድማማችነት እንዲጠናከር ከማድረግም ባለፈ ቋንቋቸው ፣ባህላቸው እንዲሁም በክልሉ ያሉ ጸጋዎች ለሌሎች ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል ይፈጥራል ብለዋል።
ዘንድሮ 20ኛው የኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት በሚል መሪ ቃል በክልሉ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል ብለዋል አቶ ሙስጠፋ።
በተለይም ህዝቦች በብዝሃነታቸው ውስጥ ሀገራዊ አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲዘልቁ በሚያግዙ ሁነቶች ላይ ልዩ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ አመላክተዋል ።
ስለዚህም በዓሉ ለማክበር ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚመጡ እንግዶች ደማቅ አቀባበል ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
20ኛዉ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በዓል የማክበር አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ሰነድ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ አማካሪ አቶ ያሲን ሳኒ ቀርቦ ዉይይት ተደርጎበታል።
የበዓሉ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ቀን መከበሩ የሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህል፣ ቋንቋና ሌሎች ማንነቶችን በተገቢዉ እንዲታወቁና እንዲከበሩ በማድረግ ረገድ ትልቅ ፋይዳ ያለዉ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም ቀጣይ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ከልዩነት ይልቅ አብሮነትን ይበልጥ በሚያጎልብት መልኩ ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ዝናሽ ሙሉጌታ ከወልቂጤ

More Stories
ሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ እውቀት ጋር በማዋሀድ ጥቅም ላይ ለማዋል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ
የወተት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን በወላይታ ዞን የጉኑኖ ሀሙስ ከተማ አስተዳደር ገለጸ
የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በዓል የጋራ ትርክቶችን በማጉላት ልናከብር እንደሚገባ ተገለፀ