በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስራ ከ38ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት መታቀዱ ተገለጸ

በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስራ ከ38ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት መታቀዱ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስራ ከ38 ሽህ 500 ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የወላይታ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በወላይታ ዞን የአርሶአደሩን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ለግብርና ሥራ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ ሀላፊ ዶክተር ዘማች ሶርሳ ተናግረዋል።

በዞን ደረጃ በበጋ መስኖ ስራ ከ38ሺህ 583 ሄክታር መሬት በላይ ለማልማት መታቀዱን ዶክተር ዘማች ጠቁመው፥ እስካሁን ባለው ሂደት 14ሺህ 866.75 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈን መቻሉን ገልጸዋል።

1ሺህ 409.4 ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር የተሸፈነ ሲሆን በጓሮ አታክልት 32ሺህ 872.6 ሄክታር መሬት መሸፈኑ የጠቆሙት ኃላፊው፥ ከዚህ በተጨማሪ በቆሎ፣ ድቡልቡል ድንችና የመሳሰሉ ሰብሎች መሸፈኑን አብራርተዋል።

ያለ ቴክኖሎጂ የግብርና ሥራን ውጤታማ ማድረግ ፈፅሞ አይቻልም ያሉት ሀላፊው፥ ዘርፉ በቅንጅት እየተመራ መሆኑን ገልፀዋል፥ በዞኑ የምርት መጠኑን ለማሳደግ በአርሶአደሩ ዘንድ ያለውን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውስንነት ለመቅረፍ ታቅዶ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

ለውጤታማነቱ የግብርና ባለሙያዎች ጠንካራ ክትትል ሊኖር ይገባል ያሉት ኃላፊው፥ ዘርፉም በልዩ ትኩረት እንዲመራ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በወላይታ ዞን በዘንድሮ የበጋ መስኖ ሥራ ከ10 ሚልዬን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱም ተጠቁሟል።

ዘጋቢ፡ በቀለች ጌቾ – ከዋካ ጣቢያችን