የእናቶችንና ህጻናት ሞት ለመቀነስና ጤና ለማሻሻል እናቶች የቤተሰብ  እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እገዛው  የላቀ መሆኑ ተገለፀ

የእናቶችንና ህጻናት ሞት ለመቀነስና ጤና ለማሻሻል እናቶች የቤተሰብ  እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እገዛው  የላቀ መሆኑ ተገለፀ

የማዕከላዊ አትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከEngender health” የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ባለፈው አንድ ዓመት በክልሉ በእናቶች እና ህጸናት ጤና ማሻሻል ላይ ያተኮረ የፕሮጀክት አፈጸጸም ስራዎችን ገምግሟል።

በማዕከላዊ  ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ  የእናቶችና ህጻናት እንዲሁም የወጣቶች እና የአፍላ ወጣቶች ጤናና ስርዓተ ምግብ አገልግሎት ዳይሬክተሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሌጅሶ እንደተናገሩት በክልሉ የእናቶችን ጤና ለማሻሻል እና ሞት ለመቀነስ የተለያዩ የጤና አደረጃጀቶችን በመጠቀም እናቶች ተገቢ የጤና ክትትል እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው ብለዋል።

 የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በተገቢው ተግበራዊ ከተደረገ የእናቶች ሞት መጠን 40ከመቶ የህጻናትን ሞት ደግሞ 13 ከመቶ መቀነስ እንደሚቻልም አቶ ተስፋዬ ጠቅሰዋል።

አንዲት እናት ከወለደች በኃላ ለቀጣይ  እርግዝና ዝግጁ  ለመሆን  ቢያንስ ሁለት ዓመት ቆይታ ልጆችን በአግባቡ እንዲትንከበከብ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ፋይዳው የላቀ እንደሆነም አቶ ተስፋዬ አመልክተዋል።

በጤና ሚኒስቴር የስነ-ተዋልዶ ቤተሰብ እቅድና አፋላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ፕሮግራም ኃላፍ ዶ/ር አለማየሁ ሁንዱማ የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የተለያዩ  ፕሮጀክቶች ተቀርጾ ተግባራዊ  እየተደረገ  ይገኛል  ብለዋል።

እናቶች የቤተሰብ  እቅድ  አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን የሞት ምጣኔ ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አንስተዋል።

 እንደሀገር በ2030 በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችና ህጻናት ሞት መጠን ከ100ሺህ ወደ አንድ መቶ አርባ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር አለማየሁ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን እናቶች እንዲጠቀሙ ግንዛቤ እየተፈጠረ እንደሆነም አንስተዋል።

በ”Engender Health” የሲዳማ፣የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ኤርዶሎ እንደገለጹት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ  ክልል በከፍተኛ ደረጃ የወሊድ ምጣኔ ላይ በሚገኙ ጤና  ተቋማት ያከናወናቸውንና የመጡ ለውጦች ታሳቢ ያደረገ መድረክ ነው ብለዋል።

 በክልሉ የቤተሰብ እቅድ  ተጠቃሚነትን ለማሳደግና ለማሻሻል በተሰራ ስራ 14 ከመቶ የነበረ የድህረ ወሊድ ምጣኔ አሁን ላይ 31 ከመቶ ማሳደግ መቻሉንም አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።

በመድረኩ የ”Engender Health”ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ስዩም እንቁባህር እንደተናገሩት ድርጅቱ  የእናቶችና  ህጻናት ሞት ለመቀነስ በሀገር ደረጃ በስድስት  ክልሎች እንዲሁም መንግስት የያዘውን በ2030 ጎል ለማስፈጸም እናቶች እና ህጸናት ጤና ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ  መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ ከ3 መቶ በላይ ከፍተኛ የወሊድ ምጣኔ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሆስፒታሎች የተሻሻለ ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍና የአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለእናቶች ሞት ምክንያት የሆነውን ከወሊድ በኋላ የሚከሰተውን የደም መፍሰስ መጠን በልኬት ማወቅ የሚያስችል ከልብሬትድ የተሰኘ የምርመራ መስሪያ ሁሉም በፕሮጀክቱ የታቀፉ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች እንዲያገኙ ድጋፍ መደረጉን ዶክተር ስዩም አመልክተዋል።

ባለፈው  አንድ ዓመት ብቻ ከ8 ሺህ በላይ የጤና ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን የተናገሩት ዶ/ር ስዩም ባለፈው  አንድ ዓመት ብቻ ከ1ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የህክምና መሳሪያዎችን 1መቶ 50 ሆስፒታሎች ድጋፍ መደረጉን አክለዋል።

ዘጋቢ:-በየነ ሰላሙ ከሆሳዕና ጣቢያችን