የተማሪዎችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በርካታ ማሻሻያዎች ማድረጉን የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ በሶስት ግቢዎቹ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ስራውን እያከናወነ ይገኛል።
የግቢው ተማሪዎችም ዩኒቨርስቲው ከጊዜ ወደጊዜ ለተማሪ ውጤት መረጋገጥ የሚያደርጋቸው ጥረቶች ለውጤታማነታቸው ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ።
በተለይም የቤተ መጽሀፍት አደረጃጀት እና አጠቃቀም ስርአታቸው ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል መቻላቸው እና የቤተሙከራ ግብአቶች በተሻለ ሁኔታ እየቀረቡ መሆኑ በጥሩ ጎኑ አንስተዋል።
መምህራንም ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም የአመራር ለውጡ ስራ በግቢው ከተሰራ በኋላ የመማር ማስተማር ስራው ከጊዜ ወደጊዜ ለውጥ እንደታየባቸው ጠቁመው ለተማሪዎቹ ውጤታማነት ማነቆ የነበሩ ችግሮች እየተፈቱ መምጣታቸው ለውጥ መሆኑን ነው መምህራኖቹ የተናገሩት።
የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ተረፈ ጌታቸው በበኩላቸው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ በመማር ማስተማሩ ተግባር እና በተማሪዎች ውጤታማነት ላይ የተሻለ ተግባር ሲፈጽም መቆየቱን አውስተው ይህንን የተሻለ አፈጻጸም አጠናክሮ ለማስቀጠል ለመማር ማስተማሩ እንቅፋት የሆኑትን ችግሮች መለየት መቻሉን ጠቁመዋል።
በተለይም ከቤተመጽሐፍ እና ቤተሙከራ አጠቃቀም እና ግብአት ማሟላት ጋር ያሉ ችግሮችን የመለየት ስራ በመስራት እንዲሻሻሉ ተደርጓልም ብለዋል ።
የመምህራንን አቅም በማጎልበት ረገድ የትምህርት እድል ተጠቃሚ በማድረግ አቅማቸውን እንዲጎለብት ተሰርቷል ብለዋል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ዋቆ ገዳ በበኩላቸው በዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና የተሻለ ውጤት አምጥተው እንዲያልፉ በተሰራው ስራ 8 ከመቶዎቹን ማሳለፍ መቻሉን ጠቁመዋል።
የቤተመጽሀፍት አደረጃጀቱን በማሻሻልም ተማሪዎች እራሳቸውን በእውቀት ከፍ እንዲያደርጉ መሰራቱንም ተናግረዋል ።
የመምህራንን አቅም በማሳደግ ረገድም በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ደረጃቸውን ከፍ እንዲያደርጉ መደረጉን ጠቁመዋል ።
ተጀምረው ለረጅም ጊዜ የቆዩ የመምህራን ቤት ግንባታ በማስቀጠልም መምህራኑ ተረጋግቶ ተቀምጠው የመማር ማስተማር ስራውን እንዲያስቀጥል በተሻለ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ፡- አብዮት በቀለ ከሚዛን

More Stories
ሀገርን እና ህዝብን በተሻለ ቁመና ማገልገል ይገባል – ርዕሰመስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
የምርኩዝ እግረኞች
የዓለም የስኳር ህመም ቀን በኢትዮጵያ ለ34ኛ ጊዜ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች እየተከበረ ነው