የምርኩዝ እግረኞች

የምርኩዝ እግረኞች

በዘላለም ተስፋዬ

ኢትዮጵያ የብዝሃ ባህል ማንነት ማሰሮ፣ የአኗኗር ዘይቤ ድብልቅ፣ የዘመን ተሻጋሪ እሴት ውቅር ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም። በምትጓዙበት አራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት አይንን ሰቅዞ የሚይዝ፣ ቀልብን የሚገዛ፣ መንገደኛ መሆንን አስረስቶ ትኩረትን የሚያሸፍት የአንዳች አይነት ክስተት ማዕከል ናት፤ ኢትዮጵያ !።

በበናዎች ሰማይ ስር የፊዚክስ ቀመር፣ የተፈጥሮ ህግና ዘመናዊ ሳይንስ መሳ ለመሳ ቢራመዱ አይግረምህ። በናዎች ከሚታወቁባች በርካታ ባህላዊ እሴቶች መካከል ‘በምርኩዝ/መቆሚያ ምሰሶ እግረኛነታቸው በአየር ላይ የሚያደርጉት ጉዞ’ የብዙሐኑን ቀልብ የሚስብ ነው። አካላዊ ቅልጥፍና፣ ጥንካሬና ሚዛን መጠበቅ (Flexibility, Balance and Physical strength) ባልተስማማ ወጣ-ገባ ስነ-ምህዳር እንደ ግልገል እንቦሳ ሲዘሉና እንዳሻቸው ሲፈነጩ ለታዘበ የጉድ ነው።

መኖሪያቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በታችኛው የኦሞ ሸለቆ በወይጦ በረሃ እና ኦሞ ወንዞች መካከል ሲሆን፥ በና ጸማዮች የኑሮ መሠረታቸው በዋናነት እርባታ እና አነስተኛ የእርሻ ስራ ነው።

በጣም የሚገርመው ታሪካቸው ከመሬት ከፍታ አየር እየቀዘፉ በምርኩዝ እንዲራመዱ ያደረጋቸው፥ ራሳቸውን ከአደገኛ አውሬ ለመከላከልና ከእባብ ንክሻ ወይም መነደፍ ለመጠበቅ መሆኑን ያነጋገርኳቸው የአከባቢው ነዋሪውች ይገልጻሉ።

ቀደም ባለው ጊዜ የብሔሩ ወጣቶች ከብት ለማገድ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ተደጋጋሚ የዱር እንስሳት ጥቃትና ጉዳት ይደርስባቸው ነበር። ከዚህ ችግር ለማምለጥ ሲባል ከረዣዥም ዛፎች መርገጫ ያለው የተመለመለ ምርኩዝ/ምሰሶ በማዘጋጀት በከፍታ ላይ ሆነው አየሩን እየቀዘፉ እንደልባቹ ይራመዳሉ።

በዚያን ዘመን አያቶቻቸው ለችግራቸው ማምለጭ የፈጠሩት ስልት አሁን የአከባቢው ልዩ መለያና የቱሪስት መስህብ እስከመሆን ደርሷል።

በረዣዥም የእንጨት ምርኩዞች ላይ መራመድ በማህበረሰቡ አባላት ዘንድ የቆየ ባህላዊ እሴት ሆኗል።

በስፋት ያላጋቡ ወጣት ወንዶች በዚህ አይነቱ የማህበረሰብ ልማድ ውስጥ በስፋት ጎልተው የሚታዩ ሲሆን፥ የበዓላት ሰሞንና አንዳች አይነት ባህላዊ የአምልኮ ሥርዓቶች በሚፈጸምበት ወቅት፥ ወጣቶቹ በነጭ ቀለም አምረውና ተውበው፣ በቄንጠኛ መስመሮች ሰውነታቸውን አስጊጠው፤ በምርኩዝ እንጨት የተለያየ አይነት ዳንስና ትርኢት በማሳየት ዝግጅቱን ያደምቃሉ።

የመረማመጃ የእንጨት ምሰሶ(ቋሚዎችን) ለመሥራት የሚያገለግሉ የዛፍ አይነት በስፋት በአካባቢያቸው ያገኛሉ። ታዲያ ለዚሁ አላማ የሚውለውን ምሰሶ ለማዘጋጀት (ቁመቱ እንዳስፈላጊነቱ ብዙ ሜትሮች ሊረዝም ወይም ሊያጥር ይችላል) ብዙ እውቀት፣ ሚዛንን እና አካላዊ ጥንካሬን ይጠይቃል።

በሚገርም ሁኔታ ግን ይህ ለበና ወጣቶች በሚያስደንቅ ውበት እና ቅልጥፍና በምሰሶው ላይ ወጥተው ሲራመዱበት ያላቸውን አካላዊ ጥንካሬ እና የአካል ብቃት ለመገመት አይቸገርም።

የተወሳሰበ የእግር ስራ፣ ዳንስ መሰል እንቅስቃሴዎችን እና የአክሮባት ትርኢቶችን ሲያከናውኑ እንደ እኔ እግር ጥሎት ለታዘበ መንገደኛ በእጅጉ ይገረማሉ።