የዓለም የስኳር ህመም ቀን በኢትዮጵያ ለ34ኛ ጊዜ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች እየተከበረ ነው

የዓለም የስኳር ህመም ቀን በኢትዮጵያ ለ34ኛ ጊዜ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች እየተከበረ ነው

ሀዋሳ: ሕዳር 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዓለም የስኳር ህመም ቀን በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ “የስኳር ህመምና ደህንነት፤ በስራ ቦታ ስለ ስኳር ህመም ይበልጥ ይገንዘቡ ተጨማሪ ድጋፍ ያድርጉ ” በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው፡፡

የዓለም የስኳር ህመም ቀን በየአመቱ ህዳር 5 በዓለማቀፍና በሀገርአቀፍ ደረጃ ሲከበር ስለ ስኳር በሽታ፣ ስለበሽታው መከላከል እና የተሻሻለ የስኳር ህክምና አገልግሎትን አስፈላጊነት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

የቀኑ መከበር በተለይ የስኳር ህመም በአለም ዙሪያ ባሉ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች እና ማህበረሰቦች ላይ የሚኖረውን ከፍተኛ ተጽእኖ ለማስታወስና ሁሉም ሰው ስለ ህመሙ በቂ እውቀትና ግንዛቤ እንዲይዝ ያስችላል ተብሏል።

በሀዋሳ ሪፈራል ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሀኪምና የሪፈራል ሆስፒታል ጥራትና ቁጥጥር ዳይሬክተር ዶ/ር ገነት አማረ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የስኳር ህመም በሁሉም ዕድሜ ሊያጋጥም የሚችል የጤና ችግር መሆኑን ገልፀው፥ ህመሙ ለተለያዩ ተጓዳኝ የጤና ችግሮች እንደሚዳርግ ጠቁመው፥ በሆስፒታሉ ከህፃናትና አዋቂ ክፍል አስተባባሪዎች ጋር በመቀናጀት ቀኑን አስመልክቶ ግንዛቤ በመፍጠር በውይይት እየተከበረ መሆኑን ጠቁመዋል።

የምንሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል የታካሚዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ገነት፥ ከስኳር ህመም ታካሚዎች ጋር በቅንጅት መስራት ስለ ችግሩ በስፋት የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ያስችላል ብለዋል።

የሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ለስኳር ህሙማን የሚሰጠውን አገልግሎት የበለጠ የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ያስረዱት ዶ/ር ገነት፥ የህፃናትም ሆነ የአዋቂዎች የተመላላሽ ህክምና ለብቻው እየተሰጠ ሲሆን በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለማብቃት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የውስጥ ደዌ ሀኪም የሆነው ዶ/ር አንተነኽ ጥላሁን በበኩሉ በሰጠው አስተያየት፥ በተለይ በህፃናት ላይ የሚከሰተው የስኳር አይነት፥ ወላጆች ምልክቱን በቅርበት በመለየት ተገቢውን የህክምና ክትትል በማድረግና የልጆቻቸውን የአመጋገብ ስርአት በማስተካከል ጤንነታቸው እንዲጠበቅ ሊያግዙ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሃዋሳ ስኳር ህሙማን ማህበር አባላት ቀኑን አስመልክቶ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ያላቸውን ግንዛቤ የበለጠ እንዳሳደገው ገልፀው፥ ለችግሩ የተሰጠው ትኩረት በዚህ ልክ ከፍ ብሎ በማግኘታው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

በዓለማችን ግማሽ ያህሉ ታማሚዎች የስኳር ህመም እንዳለባቸው ባለማወቃቸው መድሀኒት እንደማይወስዱ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።

በ1990 የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 200 ሚሊየን የነበረ ሲሆን በ2022ደግሞ 830 ሚሊየን ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ