በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚሠሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር የማህበረሰቡን ሕይወት በዘላቂነት ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታወቀ

በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚሠሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር የማህበረሰቡን ሕይወት በዘላቂነት ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታወቀ

ቢሮው በቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በመስኖ ተቋማት በተከናወኑ ተግባራት እና በፕሮጀክቱ 2018 በጀት አመት የተከለሰ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዲመካ ከተማ መክሯል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልክት አስተላልፈው፤ የቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በመጀመሪያው ምዕራፍ ትግበራ የዞኑን አርብቶ አደር የሚለውጡ በርካታ ሥራዎች ማከናወኑን ገልፀው ፕሮጀክቱ በቀጣይ ምዕራፉ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የክልሉ አርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሚሊዮን ተክሌ የ2018 በጀት አመት የተከለሰ ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፤ ፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ ያከናወናቸውን ተግባራት በማጠናከር ተጨማሪ ተግባራትን በሁለተኛው ምዕራፍ በማከል የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤካል ኔትር፤ በመስኖ ተቋማት ላይ ያሉ አፈፃፀሞችን በማጠናከር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ገልፀው ቢሮው የአርብቶ አደሩን ሕይወት በዘላቂነት ለማሻሻል በሚያደርገው ጥረት የዳሰነች ወረዳን መልሶ ማቋቋምና የሆስቴል አገልግሎት አሰጣጥን ማሳለጥ ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል።

በውይይት መድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ በባለቤትነት በቅርበት ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን