ጤናማ፣ ደስተኛ እና አምራች ቤተሰብን ለመፍጠር በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ አሉታዎችን ማረም እንደሚገባ ተገለፀ
በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ዙሪያ ወንዶች አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባም ተጠቁሟል።
”ቫሴክቶሚ – ወንዶች ለትዳር አጋሮቻቸው ያላቸውን ፍቅር ማሳየት!” በሚል መሪ ሀሳብ የዓለም “የቫሴክቶሚ” ቀን በዓል በአርባምንጭ ከተማ ተከብሯል፡፡
”ቫሴክቶሚ” ለወንዶች አስተማማኝ፣ ከ99 ከመቶ በላይ ውጤታማ እና ቋሚ የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ከመሆኑም በላይ በስነ-ተዋልዶ ጤና ላይ እና በቤተሰብ እቅድ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከፍተኛ ሚና አለው::
በጋሞ ዞን የቦንኬ ወረዳ ነዋሪዎች ከሆኑት መካከል አቶ ካርቦኔ ካትሴ እና እርብቄ ካትሴ ጤናማና እና አምራች ዜጋ ለመፍጠር በማሰብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አውስተው፤ ይህም በቤተሰባቸው ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ መፍጠሩን አረጋግጠዋል ።
የዓለም “የቫሴክቶሚ” ቀን በአርባምንጭ ከተማ በተከበረበት ወቅት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ደስታ ጋልቻ፤ አገልግሎቱን በማስፋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ያሻል ብለዋል።
በጋሞ ዞን ጤና መምሪያ የእናቶች እና ህጻናት ጤና እና የስርዓተ-ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አጥናፉ አበራ እንዳሉት፤ በዞኑ ህብረተሰቡን በማስተማር የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ለማሳደግ ብሎም የሚስተዋሉ የግንዛቤ ክፍተቶችን ለማረም እየተሰራ ይገኛል ።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት መሻሻል ብታሳይም የወንዶች ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የMSI ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር አበበ ሽብሩ ናቸው።
በዓሉን ስናከብር የጋራ ኃላፊነትን በመወጣት ወንዶች በዚህም አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ወንዶች ይህንን አገልግሎት በመጠቀም አርዓያ እና አጋር እንዲሆኑ መደገፍ እንደሚገባ የተናገሩት ዶክተር አበበ፤ አቅም በማጎልበት የተማረ፣ ጤናማ፣ አምራች፣ ደስተኛ እና ውጤታማ ቤተሰብ ለማፍራት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
በኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር የስነ ተዋልዶ፣ የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት እና የአፍላ ወጣቶች ጤና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሞቱማ በቀለ፤ አገራችን የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን ተግባራዊ አድርጋ እየሰራች እንዳለ አውስተው ባንፃሩ ወንዶች ለሚስቶቻቸው የሚያሳዩት አጋርነት ሊያድግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ለ2ኛ ጊዜ በአርባምንጭ ከተማ በተከበረው የ”ቫሴክቶሚ” ቀን በዓል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና፣ የልምድ ልውውጥ እና ውይይት ተደርጓል።
በመርሀ ግብሩ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
ጤናማ፣ ደስተኛ እና አምራች ቤተሰብን ለመፍጠር በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ አሉታዎችን ማረም እንደሚገባ ተገለፀ

More Stories
የዓለም የስኳር ህመም ቀን በኢትዮጵያ ለ34ኛ ጊዜ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች እየተከበረ ነው
የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ ስርጭትን ለመግታት የተያዘውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ጥሪ አቀረበ
በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚሠሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር የማህበረሰቡን ሕይወት በዘላቂነት ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታወቀ