በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የጌዴኦ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አሳሰበ‎

በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የጌዴኦ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አሳሰበ

‎መምሪያው የዓመቱን የነጭ ሪቫን የሴቶች ቀንና ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን “ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡

‎በሴቶችና ሕፃናት የሚደርሱትን ጥቃቶች ለመከላከል ከፍትህ ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን በበዓሉ ንግግር ያደረጉት የጌዴኦ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ተወካይና የሴቶችና ሕፃናት መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪ አቶ ዮሐንስ አሰፋ ተናግረዋል፡፡

‎ከፍትህ ተቋማት ጥምረት ጋር በመቀናጀት በሴቶችና ሕፃናት ላይ ጥቃት ተፈፅሞ የሚመጡ ጉዳዮች በአጭር ጊዜ መረጃ ተጣርቶ በአጥፊዎች ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ክትትልና ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ዮሐንስ ገልፀዋል፡፡

‎አክለውም ቡድን መሪው በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

‎በበዓሉ በእንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዞኑ ህብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ዘመናይ ሕርባዬ፤ ህጻናት የሚደርስባቸውን ጥቃት መከላከልም ሆነ በግልጽ መናገር ስለማይችሉ በቅርበት በመከታተል ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።

‎ጥቃት ፈጻሚ አካላትን ለሕግ አሳልፎ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ወ/ሮ ዘመናይ አሳስበዋል።

‎በዓሉን አስመልክቶ ሰነድ ያቀረቡት የመምሪው ባለሙያ አቶ ንጋቱ አሰፋ፤ በሴቶች፣ በህፃናትና በአካል ጉዳተኞች የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል በዓለም አቀፍና በሀገራችን የወጡትን ህጎች በአግባቡ በተግባር ላይ በማዋል ሁሉም መዋቅር ከወትሮው ይልቅ በትጋት እንዲሠሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

‎ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በዞኑ የቡሌ ወረዳ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው፤ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል ከትምህርት ቤቶች፣ ከባህላዊና ሀይማኖታዊ ተቋማት፣ ከፍትህ ጥምረትና ከሌሎች አካላት ጋር በመቀናጀት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‎ከይርጋጨፌና ከቡሌ ትምህርት ቤቶች በበዓሉ ከታደሙት ተማሪዎች ዱሬቲ አሸናፊና ወልደሰንበት ንጉሴ በትምህርታቸው በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል በሚኒ ሚዲያና በሕፃናት ፓርላማ በስፋት በመወያየት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‎ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን