በክልሉ የተከሰተውን ማርበርግ ቫይረስ ለመከላከል እየተሠራ ላለው ተግባር የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ሊመሰገን ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

በክልሉ የተከሰተውን ማርበርግ ቫይረስ ለመከላከል እየተሠራ ላለው ተግባር የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ሊመሰገን ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ የተከሰተውን ማርበርግ ቫይረስ ለመከላከል እየተሠራ ላለው ተግባር የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ሊመሰገን ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች የተመራ ልዑክ በጂንካ ከተማ የቫይረሱን ቁጥጥርና መከላከል ስራ በአካል ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል።

በድንገት የተከሰተውን የማርበርግ ቫይረስ በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በተዋረድ ሥራውን ከሚያስተባብሩ አካላት ጋር በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ አብራርተዋል።

በቫይረሱ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች መጽናናትን ሚኒስትሯ ተመኝተው፤ በጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶችን ተፈፃሚ በማድረግ የመከላከሉ ተግባር ላይ ትኩረት እንዲሰጥ በአጽንኦት አሳስበዋል።

የህክምና ቁሳቆሶች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ሚኒስትሯ ገልፀው፤ በጂንካ ከተማ በተገኙበት ወቅትም ተጨማሪ በርካታ የህክምና ግብዓቶችን በስጦታ መልክ አበርክተዋል።

ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ከጤና ሚኒስትርና ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል የሚተላለፉ መረጃዎችን ብቻ ህብረተሰቡ መከታተል እንዳለበት በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለፁት፤ የቫይረሱ መከሰቱ ከተረጋገጠ ጊዜ ጀምሮ የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ባለሙያዎችን ወደ ሥፍራው በመላክ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።

በክልሉ ድንገት የተከሰተው የማርበርግ ቫይረስ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትል የክልሉ መንግስት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ምላሽ እየሰጠ እንደሆነም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደቀጠለ ሲሆን በአጭር ጊዜ ቫይረሱን ለመቆጣጠር እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል አቶ ጥላሁን።

በክልሉ መንግስት በኩል በርካታ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ እየተደረገ እንዳለም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

ልዑካኑ በጂንካ ጠቅላላ ሆስፒታል የቫይረሱ ቁጥጥር ስራን ምልከታ አድርጓል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን