ከልጅነቴ ጀምሮ የግብርና ሥራ ሱሴ ነው ! ማሳዬን በቀን ሦስት፣ አራት ጊዜ ካልጎበኘሁኝ ያመኛል – ሞዴል አርሶአደር አቶ ኮቾ ከተማ‎

ከልጅነቴ ጀምሮ የግብርና ሥራ ሱሴ ነው ! ማሳዬን በቀን ሦስት፣ አራት ጊዜ ካልጎበኘሁኝ ያመኛል – ሞዴል አርሶአደር አቶ ኮቾ ከተማ‎

‎ነዎሪነታቸው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በዳውሮ ዞን ከጪ ወረዳ ከጪ ቱታ ቀበሌ ውስጥ ነው። አቶ ኮቾ ዕድሜያቸው 60ዎቹ መጀመሪያ ቢሆንም የግብርና ስራ ሲሰሩ እንዲሁም አጠቃላይና ተክለ ሰውነታቸው አትኩሮ ላጤነው 30ዎቹን እንኳን ያጋመሱ አይመስሉም።‎

‎አቶ ኮቾ በአከባቢያቸው ብሎም በወረዳው እጅግ አርአያ የሆኑ ሞዴል አርሶአደር ናቸው። ኑሮአቸውም የተደላደለ ነው፤ እቤታቸው መግቢያ ጀምሮ ያለው ግቢያቸው እጅግ፣ ማራኪ፣ ውብና ጽዱ ነው። እንደዚሁ በአነስተኛ መንደር የተገነባ ነው ለማለት የሚከብድ መኖሪያ ህንፃ ቤት አላቸው። በሞዴል አርሶአደሩ ወደ ሁለት ሚልዮን የሚጠጋ ገንዘብ አውጥቶ የገነቡት ቤት በውስጡ አራት መኝታ ቤት፣ የእንግዳ ማረፊያ፣ ሰፊ ሳሎን፣ መፀዳጃና ሻዉር ቤት በውስጡ ያካተተ ነው።‎

‎በአጠቃላይ ቤቱ በአንድ በትንሽ መንደር ውሰጥ በሚገኝ በአርሶአደር የተገነባ ሳይሆን በአንድ ኢንቨስተር አልያም በአንድ ፋብሪካ ባለቤት የተገነባ ቤት ይመስላል። ምክንያቱም ምንም ያክል ገንዘብ ቢኖር ለግንባታው የሚሆን ቁሳቁስ እስከ ቦታው ማምጣቱ እንድሁም ዲዛይኑን ጨምሮ ሙያተኛውን ማግኘት ከፍተኛ ትዕግስት፣ ብልሃትን ይጠይቃል።‎

‎አርሶአደር ኮቾ እጅግ ሰፊ ማሣ አላቸው በማሣቸው እንደወቅቱ አፈራርቀው ሰብል ያመርታሉ። በአሁኑ ወቅት በመኸር እርሻ ያለሙት ዋና ዋና ሰብሎች ስንዴ፣ ጤፍ፣ አተር፣ ባቄላና ሌሎች ሰብሎች በማሣ ላይ ስታዩ በጥንቃቄና ትኩረት ተሰጥቶ መመረታቸውን ይመሰክራሉ። በእንስሳትም በኩል ከዶሮ ጀምሮ በርካታ የሚታለቡ ጥገት ላሞች፣ በርካታ ጥማድ በሬዎች፣ የጋማ ከብቶች፣ ለቁጥር የሚያዳግቱ በግና በፍየሎች ከእርሻ ስራ ጎን ለጎን አርብተዋል።‎

‎ታዲያ የከብቶቹን ቤት ከመኖሪያ ቤታቸው ተለይቶ መሰራቱ በራሱ የኮሪደር ልማት እሳቤው ቀድሞ የገባቸው ዘመናዊ አርሶ አደር መሆናቸዉን ያስታውቃል።‎

‎ሞዴል አርሶአደር ኮቾ በትምህርት በኩል ፊደል የቆጠሩ ባይሆኑም ልጆቻቸውን አስተምረው ዶ/ር፣ ኢንጂነር በአጠቃላይ በቁጥር ዘጠኝ ልጆችን ካፈሩት ሁሉንም አስተምሮ ለቁም ነገር ያደረሱ አባት ናቸው።‎

‎ሞዴል አርሶአደር ኮቾ በአከባቢው የሚገኙ ወጣቶች በአልባሌ ሥፍራ እንዳይውሉ እንደየዝንባሌያቸው በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ አንጡራ ሀብታቸውን ከማፍሰስም ባሻገር በአባትነት ተከታትሎ በመገሰጽ ወደ ስራ መስመር አስገብተዋል። እንዲሁም በትምህርታቸው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለሚገቡ በተለይ ወላጅ ለሌላቸው ተማሪዎች ሰንቆ በማስተማር አባታዊ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ የሚገኙ ምስጉን መሆናቸውን ብዙዎች ይመሰክራሉ።‎

‎ሞዴል አርሶአደር ኮቾ በማህበራዊ ሆነ በፖለቲካዊ ጉዳዮች እየተገበሩ ያለዉ ሚና ቀላል አይደለም፤ ከደርግ ሥርዓተ መንግስት ጀምሮ የቀበሌ ሊቀመንበር በመሆን የአካባቢያቸውን ሠላም በማስከበር እንዲሁም በአከባቢው ትምህርት ቤት እንዲከፈትና ሌሎችም ልማቶች እንደኖሩ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። አሁንም እየተገበሩ ይገኛሉ።‎

‎በቤተ እምነትም የኃይማኖት መቻቻል እንዲኖር በተሰጣቸው ሃላፊነት የቤተክርስቲያን ሽማግሌ በመሆን ወጣት አገልጋዮችን በመምከር፤ አዋቂዎች ጋር በመመካከር እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲኖሩ በማስተማር ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። ከዚህም ባሻገር ለቤተክርስቲያን ለአገልግሎት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ልጆቻቸውን በማስተባበር ማሟላታቸውም በብዙዎች አርአያነታቸው ተመስክሮላቸዋል።‎

‎ሞዴል አርሶአደር ኮቾ ከእሁድ በስተቀር ሙሉ ጊዜያቸውን አብዛኛውን በእርሻ ሥራ እንደሚያሳልፉ ገልፀው ፤ የሰውን ልጅ የሚያስከብረው ሥራና ሥራ ብቻ መሆኑን ባገኙት አጋጣሚ በመናገር በተለይ በማሣቸውን በቀን ሁለት ሦስት ጊዜ ተመላልሰው በውስጥ ካልተገኙ እንደሚያማቸው ይናገራሉ። ክረምት ከበጋ ሳይሉ የእርሻ ስራ በመስራት በሬዎቻቸውን በሰዓታት ልዩትት በመቀያየር መሬታቸውን ደጋግሞ በማረስ ሙሉ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዉጤታማ እንደሆኑም ያስረዳሉ ።‎

‎ሞዴል አርሶአደሩ የጥንካሬ ምንጫቸው ባለቤታቸው እንደሆኑ ደጋግመው መስክረዋል። እጅግ ስራ ወዳድ እንደሆነችና ከቤት ሥራ በተጨማሪ ሳትሰላች እርሻ ቦታ ድረስ ምግብ አዘጋጅታ በማምጣት እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦ በአግባቡ በመጠቀም የሀብት መጠናቸው እየጨምረ እንዲሄድ ትልቅ አስተዋጽኦ የተወጣች ታታሪ ሴት እንደሆነች ይናገራሉ ።‎

‎ሞዴል አርሶአደር ኮቾ እንደተግዳሩት የሚያነሱት የግብርና ስራ ዘመናዊ ለማድረግና ጊዜ፣ ጉልበት እንዲሁም ገንዘብ ለመቆጠብ በበሬ ከማረስ ወደ ትራክተር ለመቀየር እንዲሁም በአጨዳ ወቅት በሰው ጉልበት ስታጨድ የእህል ብክነት ለማስቀረት ማሽን ለማምጣት ፍላጎት ቢኖራቸውም የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር እንደሆነባቸውም አልሸሸጉም‎

አዘጋጅ፡ አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን