የወጣቶችን የስራ ፈጠራ ክህሎት ማዳበርና የፋይናንስ አቅም ማጎልበት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማንሰራራት ሚናው የላቀ መሆኑ ተገለጸ
”መተባበር ድህነት ቅነሳ” የተሠኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳና ሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ ከ250 ለሚበልጡ ወጣቶች በስራ ፈጠራ ዙሪያ የክህሎትና የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል።
በመድረኩ የተገኙት የሀዲያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምሬ ኤርሚያስ፤ ”ሀገር ቀያሪ ወጣት ነው፥ ወጣት ከተቀየረ ሀገር ይቀየራል” ብለዋል።
ወጣት መማር እና መመራመር ያስፈልገዋል ያሉት አቶ ታምሬ፤ ዓለም የተቀየረው በትጉዎች ጥረት እንደሆነም አንስተዋል።
ስራ ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በማሸነፍ ተስፋ አለመቁረጥና አሻግሮ ማየት ያስፈልጋልም ብለዋል ኃላፊው።
የነገን ራዕይ በመሰነቅና ቴክኖሎጂን ለመልካም ዕሴት በመጠቀም ለታለመለት ግብ መጽናት እንደሚገባም አቶ ታምሬ አስገንዝበዋል።
ኃላፊው አክለውም ስራ ለመፍጠር የይቻላል መንፈስ ተላብሰን ከተነሳን ውጤቱ የሠመረ ይሆናል ብለዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ”መተባበር ድህነት ቅነሳ” መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ደምሴ ሎብዱኖ እንደተናገሩት፤ ስልጠናው የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ ወደተለያዩ ሀገራት በስደት ለመኖር እየኮበለለ ያለው ወጣት በሀገሩ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ተገንዝቦ አቅሙን እንዲያጎለብት የሚያግዝ ነው።
ድርጅቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ከ3 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች በስራ ፈጠራ ዙሪያ የክህሎትና የአቅም ግንባታ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ያስታወሱት አስተባባሪው፤ በዕለቱም ከሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳና ሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ 250 ወጣቶች ስልጠናና ተምሳሌት የሆኑ ወጣቶች ተሞክሮ ማሳያ እንደተደረገም አስረድተዋል።
ስልጠናው ወጣቱን “አይቻልም” የሚለውን ዘልማዳዊ አስተሳሰብ በመቅረፍ ለለውጥ ያዘጋጃልም ብለዋል አቶ ደምሴ።
ኘሮግራሙ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪው፤ ወጣቶች ወደ ልቦናቸው ተመልሰው በታታሪነት ከሠሩ ውጤታማ መሆን ስለሚችሉ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ መክረዋል።
በመድረኩ በስራ ፈጠራ ልዩ ተሞክሮ ያላቸው ወጣቶች የስራ ልምዳቸውን ያገሩ ሲሆን የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማትም ተገኝተው የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት አብረው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የስልጠና ተሳተፊ ወጣቶችም ያገኙትን ግንዛቤ ወደ ተግባር በመለወጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በመጨረሻም በስራቸው ትጉ እና ታታሪ በመሆን ለሌሎች አርዓያ ለሆኑ ወጣቶች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ: መንግሥቱ ፊጣሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ ዙር የከፍተኛና መካከለኛ የአመራሮች ስልጠና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መሰጠት ጀመረ
የሕዝቡን አዳጊ የልማት ፍላጎት ለማሟላትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አዲስ ተሿሚዎች በትጋት ሊሠሩ እንደሚገባ በአሪ ዞን የደቡብ አሪ ወረዳ ምክር ቤት አባላት ገለፁ
የፖሊስ አባላት የኢትዮጵያን ክብርና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊሰሩ ይገባል – ርዕሰመስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)