የፖሊስ አባላት የኢትዮጵያን ክብርና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊሰሩ ይገባል – ርዕሰመስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
ሀዋሳ፣ ህዳር 10/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ)የፖሊስ አባላት የኢትዮጵያን ክብርና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰመስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ተናገሩ።
በክልሉ “ከጂኦስትራቴጂካዊ ኩስምና ወደታደሰ ቁመና” በሚል መሪ ቃል ለፖሊስ ሠራዊት አባላትና አመራሮች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቅቋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰመስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር ስልጠናው የሀገርን ክብር በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
የፖሊስ አባላቱ የኢትዮጵያን ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ጉዳዮች የተረዱበትና የሙያ አቅም ማጎልበቻ ያገኙበት መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ውስጥ ለአፍሪካ ምሳሌ መሆን የሚችሉ ተግባራት መከናወናቸውን አውስተው፤ እነኚህ ስራዎች እንዲቀጥሉና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጠበቅ የመለዮ ለባሹ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የፖሊስነት ሙያ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማገልገልና ፍትህን ለማስከበር የሚያስችል ነው ያሉት ርዕሰመስተዳድሩ፤ የክልሉ ፖሊስ ከህዝብ ጋር በመተባበር ሚናውን እየተወጣ መቆየቱንና አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ እድገት ያላስደሰታቸው አካላት የሀገሪቱን ልማቶች ለማደናቀፍ ጫና እየፈጠሩ እንደሆነ አንስተው ፤ በአባይ ወንዝና በቀይ ባህር ጉዳዮች ላይ ፍላጎት ያላቸው አካላት ባንዳዎችን እየተጠቀሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የፖሊስና ሌሎችም የፀጥታ አካላት ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጠሩ ሴራዎችን አክሽፈዋልም ነው ያሉት።
በቀጣይም የውስጥ ባንዳዎችን በማስወገድና የውጭ ጠላትን በመመከት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ታሪካችን የአሸናፊነትና የጀግንነት ታሪክ በመሆኑ፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነጥቁ አካላትን በዝምታ ማለፍ አያስፈልግም ሲሉ ገልጸዋል።
ኮንትሮባንድን፣ ህገ-ወጥ ንግድን እና መሰል የወንጀል ድርጊቶችን በቆራጥ የፖሊስ አባላትና አመራሮች ስራ መቀነስ መቻሉን ጠቁመው፤ ይህንን ትጋት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ፖሊስ ሠራዊት አባላት ሙያቸውን በሚያሻሽሉባቸው ጉዳዮች ላይ እየተሰራ እንደሆነ አመላክለው ፤ የፖሊስ አባላትን ቁጥር ለማሣደግ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የክልሉን ፖሊስ የሎጀስቲክስ ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ መሆኑንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
የወጣቶችን የስራ ፈጠራ ክህሎት ማዳበርና የፋይናንስ አቅም ማጎልበት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማንሰራራት ሚናው የላቀ መሆኑ ተገለጸ
ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ማቅረቧ ትክክለኛና ጊዜውን የዋጀ መሆኑን የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ
የዞኑ ሕዝብ ከማርበርግ ቫይረስ ራሱን መጠበቅ እንዲችል የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ አሳሰበ