ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ማቅረቧ ትክክለኛና ጊዜውን የዋጀ መሆኑን የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ

ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ማቅረቧ ትክክለኛና ጊዜውን የዋጀ መሆኑን የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ

ምሁራኖቹ በህብረተሰቡ ውስጥ ግንዛቤ የማስጨበጡ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ሀገራችን ከሶስት ሺ ዓመት በፊት ከአለም ጥቂት ሀያላን ሀገራት ተርታ እንድትሆን ያደረጋት አንዱ የባህር በሯ እና የባህር ኃይሏ መሆኑን ነው በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር መምህር፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶስተኛ ዲግሪ ተመራማሪ የሆኑት መምህር አማረ ፋንታሁ ታሪክን በማጣቀስ የተናገሩት።

የታሪክ ምሁሩ ኤርትራ የኢትዮጵያ አንድ ክፍለሀገር በመሆን የኢትዮጵያ አካል እንደነበረች ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ኤርትራ እራሷን ችላ ስትገነጠል በወቅቱ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የባህር በር ጥያቄ ሳይነሳ ተዳፍኖ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ሰአት ደግሞ ትውልዱ ይህንን ጥያቄ እንዲጠይቅና እንዲያውቅ መደረጉ ተገቢነት አለው ብለው ለዚህም ተጨባጭ ህጋዊ የሆኑ ማስረጃዎችና ዲፕሎማሲያዊ ሰነዶች ኢትዮጵያ እንዳላት ይገልጻሉ።

ምሁሩ ወደቡ ብቻ ሳይሆን ኤርትራም የኢትዮጵያ አንድ አካል የነበረች እና ህጋዊነት በሌለው በጥቂት ማህበረሰቦች ፍላጎት የተከናወነ የሪፍረንደም የምርጫ አካሄድ በወቅቱ የተደረገ በመሆኑ መሰረት የሌለው መሆኑን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በዩኒቨርሲቲው የስነምግባር እና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት መምህር መልካሙ ዘውዴ በበኩላቸው፤ አሰብ የኢትዮጵያ ሀብት መሆኑን ተናግረዋል።

ኤርትራም እራሷ የኢትዮጵያ አካል እንደነበረች የሚናገሩት ምሁሩ የ1908 ዓ.ም አጼ ሚኒሊክ እና ጣሊያን የተፈራረሙት ውል ገዢ ማስረጃ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጣሊያን ከኤርትራ ተሸንፋ ስትወጣ ይዛ የነበረችውን በሙሉ ለኢትዮጵያ መመለስ እንዳለባት ስለሚያሳውቅ ይህም በቂ ማስረጃ ነው ይላሉ። ከዚያም ባለፈ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት እንዴት የባህር በር መጠቀም እንዳለባቸው በተባበሩት መንግስታት የተቀመጠ አቅጣጫም አንዱ ማስረጃ ነው ይላሉ።

ስለዚህ ኢትዮጵያ እየጠየቀች ያለችው የባህር በር ጉዳይ ወቅቱን የዋጀና ተገቢነት ያለው መሆኑን ነው ምሁራኖቹ የተናገሩት።

ይህንንም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጡ ስራ በተገቢው መሰራት እንዳለበት አስታውቀዋል።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን