ሀዋሳ፡ ሕዳር 09/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወባ በሽታ አስከፊነቱን በመገንዘብ የመከላከልና ቁጥጥር ስራ በማህበረሰቡና በጤና ተቋማት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ጤና ጣቢያ ያገኘናቸው ተገልጋዮች ተናገሩ።
በዜጎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለው የወባ በሽታን ለመከላከል ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ለቁጥጥር ስራዎች ትኩረት በመስጠት ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት አስታውቋል።
በከተማው በሚገኙ ጤና ጣቢያ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት የመጡ ተገልጋዮች በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በከተማው በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች እምብዛም እንደነበሩ ገልፀው÷ ይሁንና አሁን ላይ በየአካባቢው በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች መበራከታቸውን ተናግረዋል።
ተገልጋዮችም የወባ በሽታ የአከባቢን ንፅህና ባለመጠበቅ በተለይ ለወባ ትንኝ መራቢያ የሚሆኑ በግንባታዎችና በዙሪያቸው ውሃ ሊይዙ የሚችሉ ቁሶቁሶችን በመከልከል እና በማፋሰስ ጤና ባለሙያዎች ጋር ሲሰሩ እንደነበር አንስተዋል ።
በጤና ተቋሙ ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ የሚገልፁት ነዋሪዎቹ የእስካሁኑ የተሻለ ቢሆንም ካለው ፍላጎት አንፃር አገልግሎቱ ከፍ ማለት እንዳለበትና ለቁጥጥርና ለመከላከል ስራዎች ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አክለዋል ።
በጤና ጣቢያው የላብራቶሪ ክፍል ባለሙያ ወ/ሮ ድንቅነሽ እና የመድሃኒት ክፍል አስተባባሪ የሆኑት ታምራት ሽብሩ በበኩላቸው ለህክምና ወደ ጤና ተቋሙ ከሚመጡ ሰዎች መከከል አብዛኞቹ በወባ በሽታ ሳቢያ መሆኑን ገልፀው ተቋሙም በተቻለው መጠን ለተገልጋዩቹ ህክምና እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ከህክምና እና ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ ከሚከሰቱ ውስንነቶች ውጭ እጥረት እንዳልገጠማቸው የገለፁት ባለሙያዎች÷ ሁሉም ዓይነት የመድሃኒት አቅርቦት አሁን ካለው መጨመር እንዳለበትና ለቁጥጥር ትኩረት መሰጠት እንደሚገባ አስታውሰዋል ።
በበሽታው የተያዙ ሰዎቹ ሲኖሩም ከመጡበት አከባቢ ጋር የመረጃ ልውውጡን በማጠናከር የክትትል ስራዎች እንደሚያደርጉ ገልፀዋል ።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት የኃላፊ ተወካይና የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ብሩክ ተስፋዬ በዜጎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለውን የወባ በሽታ ለመከላከል ግንዛቤ ከመፍጠር በለፈ ለመከላከል ለቁጥጥር ስራዎች ትኩረት በመስጠት ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል ።
በሽታው አኖፌለስ በተባሉ የትንኝ ዝርያዎች አማካኝነት የሚተላለፍ ሲሆን በሴቷ ትንኝ ንክሻ ሳቢያ ከህመምተኛ ወደ ጤነኛ ሰው የሚተላለፍ በመሆኑ የአከባቢን ንጽህና መጠበቅ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን ማፈሰስ የህመም ምልክቶች ሲስተዋሉ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት መቅናት ይገባል ብለዋል።
በጤና ተቋማት ከሎጂስቲክ እና ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ ከዞንና ከክልል ጤና ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አቶ ብሩክ አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የዞኑ ሕዝብ ከማርበርግ ቫይረስ ራሱን መጠበቅ እንዲችል የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ አሳሰበ
የከተሞች ፎረም የልምድ ልውውጥ የሚደርግበት መድረክ ነው – ተሳታፊዎች
በልማትና በመልካም አስተዳደር የሚነሱ ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ