የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ባህል፣ ማንነትን ቅርስን ከማስተዋወቅ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የዳውሮ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ገለፁ
በዞኑ የብሔር ብሔረሰቦች በዓልን በየመዋቅሮች በድምቀት ለማክበር የሚያስችል የግዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለወረዳ ባለድርሻ አካላት ተሰጥቷል።
“ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በተሻለ ሁኔታ ለማክበር በዞን ደረጃ የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ ተካሂዷል።
በዓሉ በየደረጃ ባሉ ትምህርት ቤቶችና ቀበሌዎች በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ በወረዳዎች ማጠቃለያ የውይይት መድረክ እንደሚካሄድ የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ዳዊት ሚኖታ ገልፀዋል።
ህገመንግስቱ ከፀደቀበት 1987 ዓ.ም ጀምሮ የራስን ባህልና ቋንቋ ከማሳደግና ከማስተዋወቅ ረገድ የብሔረሰቦች ቀን በዓል አከባበር የተሻለ ጠቀሜታ እንዳበረከተ አንስተው፤ ይህንንም ሁሉም ዜጋ የበአሉን ትሩፋት በመረዳት እንዲያከበር እስከታችኛው መዋቅር የማስገንዘብ ሥራ በትኩረት እንዲፈፀም እየተሠራ ነው ብለዋል።
የበዓሉን አከባበር የሚያስፈፅሙ ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንዲመሩት ለማስቻል የአሰልጣኞች ስልጠና ስለመዘጋጀቱ የጠቆሙ ሲሆን የብሔር ብሔረሰቦች በዓልን በህገመንግስቱ እንደብሔር ያገኘናቸውን ትሩፋቶች በመዘከር፣ አቅመ ደካሞችን በማገዝ፣ የአካባቢ ፅዳት በመስራትና መሰል በጎ አድራጎት ተግባራትን በመፈፀም ማክበር እንደሚገባ ገልፀዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት የህግ ማውጣት፣ ጥናትና ምክር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ገበየሁ በመድረኩ የስልጠና ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት፤ “የበዓሉ መከበር ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውን፣ ታሪካቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያለሙ፣ እንዲጠብቁና እንዲያስተዋውቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የብሔር ብሔረሰቦችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከለውጡ መንግስት ወዲህ በርካታ ስራዎች እየተተገበሩ መሆናቸውን በመግለፅ፤ በየአካባቢው የተመሰረተው የባህላዊ ዳኝነት ስርዓት እያደገ የመጣውን የበጎ አገልግሎት ተግባራትን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡም የህገመንግስትና ፌደራሊዝም ዕውቀቱን እንዲያሳድግ በማህበረሰብ ቋንቋዎች የሚያስተላልፉ ሬዲዮ ጣቢያዎች ጭምር የማስገንዘቡ ሥራ በክልሉ በኩል በትኩረት እየተሠራ እንዳለም አቶ ተመስገን አክለዋል።
በቀጣይም ቢሆን ለዘርፉ የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት በመጠቀም ገዥ ትርክቶችን ለትውልዱ በማስረፅ ብዝሃነትን ያቀፈ አንድነትን ማሳደግ ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑንም አብራርተዋል።
ሁሉም ዜጋ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተግባራት ላይም የድርሻቸውን ድጋፍ በማጠናከር ሀገራዊ ጉዳዮችን የጋራ አጀንዳ አድርጎ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል።
የበዓሉ አከባበር ቋንቋ፣ ማንነትና ቅርስን እኩል ከማስተዋወቅና ከማልማት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
የብሔር ብሔረሰብ በዓልን በትምህርት ቤቶች ጥያቄና መልስ ውድድር በማካሄድ፣ በበጎ አገልግሎት እና በህገመንግስ ዙሪያ ግንዛቤ በማስረጽ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ማድረጋቸውን ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡
ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች በተለያዩ ዝግጅቶ እየተከበረ በመጨረሻም እንደሀገር አቀፍ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እንደሚከበርም ይታወቃል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን

More Stories
ብልጽግናን ለማረጋገጥ የፖሊስ አመራር እና አባላትን አቅም ማሳደግ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ህዳር 29 ለሚከበረው የ20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል የአሰልጣኞች ሥልጠናና ማስፈፀሚያ ዕቅድ ላይ የውይይት መድረክ በካራት ከተማ እየተካሄ ይገኛል
በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን ተጠቅሞ በመስራት ከህገወጥ ስደትና ከድህነት መላቀቅ እንደሚገባ ተገለጸ