በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን ተጠቅሞ በመስራት ከህገወጥ ስደትና ከድህነት መላቀቅ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 07/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን ተጠቅሞ በመስራት ከህገወጥ ስደትና ከድህነት መላቀቅ እንደሚገባ በከብት እርባታ ዘርፍ የተሰማሩ ከስደት ተመላሽ ወጣቶች ተናገሩ
በከተማ ግብርና ዘርፍ በግል ሆነ በማህበር ተደራጅተው ለሚሰሩ ዜጎች አስፈላጊ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸው የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
አቶ ብርሃኑ አዴቦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ያልፍልኛል ብለው ወደ ደቡብ አፍሪካ ተሰደው እንደነበር ገልጸው÷ የስደት አስከፊነትን በመረዳት ወደ ሀገራቸው በመመለስ በ2009 ዓ.ም የቤተሰብ አባላትን በመያዝ በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው በ150 ሺህ ብር ካፒታል እና በሁለት የወተት ላሞች ከመንግስት ባገኙት መሬት የከብት እርባታ ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከወተት ከብት እርባታ ስራ በተጨማሪ በድለባ፣ በካፌና በእንስሳት መኖ አቅርቦት ስራ ላይ በመሰማራት ውጤታማ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ብርሃኑ በስራቸው ከዞን እስከ ፌዴራል ደረጃ ተሻላሚ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ከኢንተርፕራይዝ ወደ ኢንቨስትመንት ለመሸጋገር በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው በአካባቢው የመሰረተ ልማት አላመሟላትና የመሬት ጥበት መኖሩንም አስረድተዋል።
በቀጣይ የወተት ማቀነባበሪያ ለመጀመር በማቀድ ከልማት ባንክ ጋር በመሆን እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ገልጸዋል ።
የአባታቸውን ፈለግ በመከተል ከስደት ሀገር በመመለስ በኢንትራፕራይዙ አባል በመሆን እየሰራ ያለው ወጣት መልካሙ ብርሃኑ በበኩሉ ማንም ሰው በአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በመረዳትና ተግቶ በመስራት ውጤታማ መሆን እንደሚችል ገልጿል ።
አቶ አንተነህ በቀለ የአቶ ብርሃኑ ጎረቤት ሲሆኑ ተሞክሮአቸውን በመውሰድ በአሁኑ ወቅት በወተት ከብት እርባታ ዘርፍ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
በኢንተርፕራይዙ ከ20 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል የተፈጠረላቸው ሲሆን ወጣት ዳዊት ሶዳኖ እና ዲላሞ ዲንዳሞ በሰጡት አስተያየት በማህበሩ ሰርተው ከሚያገኙት ገቢ በተጨማሪ ለወደፊት ኑሯአቸው የሚጠቅም ሙያ መቅሰማቸውን ተናግረዋል ።
አንዳንድ አስተያየታቸውን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎችም ኢንተርፕራይዙ የወተት ተዋጽኦዎችን ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ዋጋ በማረጋጋት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የአራዳ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙላቱ ወልዴና የቀበሌው ማዘጋጃ ጽ/ቤት ስራአስኪያጅ አቶ መሠረት አባ በበኩላቸው ከኢንተርፕራይዞቹ የሚነሱ የመሰረተ ልማትና የመሬት አቅርቦት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት ባለሙያና የአራዳ ቀበሌ ደጋፊ የሆኑት አቶ አርጋው ድሌቦ በበኩላቸው በዘርፉ በግልም ሆነ በማህበር ተደራጅተው ለሚሰሩ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ ከሌማት ትሩፋት ተግባራት አንዱ በሆነው በወተት ልማት ዘርፍ የተሰማሩትን መንደር በመመስረት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንና ለውጤታማነታቸው እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ ከባለድርሻ ካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አስረድተዋል።
ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በራሳቸው የሚተማመኑ፣ በሥራ ክቡርነት የሚያምኑ፣ የሙያና ክህሎት ብቃት ያላቸውን የሰው ኃይል መፍጠር ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ
የኮሌጁንና የአካባቢውን ማህበረሰብ በቴክኖሎጂ የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
የ2017/18 በመኸር እርሻ ከተዘሩ ዋና ዋና ሰብሎች የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ አልመው እየሠሩ መሆናቸዉን በዳዉሮ ዞን የከጪ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ