ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚወጡ ተመራቂ ሰልጣኞች በሰለጠኑበት ዘርፍ ሀገሪቱ ለጀመረችው የብልጽግና ጉዞ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ
የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለ22ኛ ዙር በተለያዩ የስልጠና መስኮች ያሰለጠናቸውን 5 መቶ 64 ሰልጣኞችን አስመርቋል።
በምረቃ መረሀ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ አወል ሸንጎ እንደገለጹት፤ ኮሌጁ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሰልጣኞችን በተለያዩ ደረጃዎች አሰልጥኖ በማውጣት ላይ ይገኛል።
በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በኢንደስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን የማሳደግ ስራ በኮሌጁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኮሌጁ በ12 የሙያ ዘርፎች የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና በመስጠት እንዲሁም በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የትብብር ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ በእለቱ 5 መቶ 64 ሰልጣኞችን ማስመረቅ መቻሉንም አቶ አወል ጠቁመዋል።
ከተመራቂዎች ውስጥ 3 መቶ 96 ሴቶች ሲሆኑ ኮሌጁ ለአካል ጉዳተኞች የሰጠውን ነጻ የትምህርት ዕድል በመጠቀም 6 አካል ጉዳተኞች በዕለቱ መመረቃቸውንም ገልጸዋል።
የዕለቱ ተመራቂዎችም በኮሌጅ ቆይታ ያገኙትን ስልጠና ተጠቅመው ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የኮሌጁ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ማቴዎስ አኒዮ በበኩላቸው፤ የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ከሚያበረከቱ ዘርፎች አንዱ የቴክኒክና ሙያ መስክ መሆኑን ገልፀዋል።
ኮሌጁ የማህበረሰቡን ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ቀድቶ ለኢንተፕራይዞች የማሸጋገሩን ስራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት አቶ ማቴዎስ፤ በዞኑ የሚገኙ ወጣቶች እና ሴቶች በኮሌጁ የሚሰጡ መደበኛና የአጫጭር ጊዜ ስልጠናዎችን በመዉሰድ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የስራ እድል መፍጠር እንዳለባቸውና የዞኑ አስተዳደርም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ተወካይና አማካሪ አቶ ነስሩ ያሲን በዕለቱ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዕለቱ ተመራቂዎች በሰለጠኑበት መስክ ለአፍታም ሳይዘናጉ ወደ ተግባር መግባት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ኮሌጁ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የጀመራቸውን ስራዎች በሁሉም የፍራፍሬ ዘርፎች ማስፋት እንዳሚገባዉ ገልፀው፤ በእንጨት ስራ እና በዶሮ እርባታ ዘርፍ በኢንተርፕራይዝ የተጀመሩ ተግባራትን ማጠናከር አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።
አንዳንድ የዕለቱ ተመራቂ ሰልጠኞች በሰጡት አስተያየት በሰለጠኑበት መስክ ስራ ፈጥረዉ በመስራት ለሀገር እድገት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።
በዕለቱም በኮሌጁ የአይሲቲ መሠረተ ልማት ማስመረቅ የተቻለ ሲሆን በኮሌጁ እየተሰሩ ያሉ የስራ እንቅስቃሴዎች ተጎብኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
ለትውልድ ግንባታ መሠረት ለሆነው የሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ምሁር-አክሊል ወረዳ በመንግስትና በህብረተሰቡ የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው
ክህሎት መር ስልጠና በመተግበር በሀገሪቱ ያለውን ፀጋ ተጠቅሞ በትጋት ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ