በፍትህና የህግ መዋቅሮች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አደረጃጀቶችን ከመፍጠር አንጻር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 05/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በፍትህና የህግ መዋቅሮች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አደረጃጀቶችን ከመፍጠር አንጻር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የደቡብ ኦሞ ዞን ሽግግር ም/ቤት አሳሰበ።
እንደ አዲስ የዞን መዋቅር በዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት በጥንካሬ የተመለከታቸው መሆኑን የዞኑ የህግ፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ አስታውቋል።
በፖሊስ፣ ፍርድ ቤትና የምክር ቤት አደረጃጀቶች የተከናወኑ ተግባራት በቋሚ ኮሚቴው ምልከታ የተደረገባቸው አብይ ተቋማት ናቸው።
በኛንጋቶም፣ ዳሰነችና በቱርሚ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የፖሊስ መዋቅሮች የተጠርጣሪ አያያዝ ላይ ከተስተዋሉ ውስን ተግዳሮቶች በቀር የተሸለ አፈጻጸም መኖሩን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢው አቶ ኡሉሉ ቻርሊኒ ገልጸዋል።
ከሁሉም በላይ በዳሰነች ወረዳና ቱርሚ ከተማ የተመለከቱት ባህላዊ የፍርድ አሰጣጥ ሂደት የወንጀል ድርጊቶች በባህላዊ ስርዓት የአካባቢ ሽማግሌዎች የሚፈቱበት መንገድ የፍትህ አሰጣጥ ከማቀላጠፍ ባለፈ የጸጥታ መዋቅሩን ጫና የሚያቃልሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በየደረጃው የተቋቋሙ የም/ቤት አደረጃጀቶች ወደ ስራ መግባታቸው በመልካም ጎኑ የሚጠቀሱ መሆኑን ጠቁመው÷ የግብአትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እንዲያሻሽሉ በማድረግ በርካታ የቤት ስራዎች የሚቀሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በአዲሱ ዞን ዘመናዊ የፍትህ ተቋማት በበና ጸማይና ሐመር ወረዳዎች ጥራታቸውን ጠብቀው እየተገነቡ መሆናቸውን ያነሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ተቋማቱ የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ የሚያዘምኑ እንደሚሆኑ ይጠበቃል ብለዋል።
ያነጋገርናቸው የቋሚ ኮሚቴው ተመላላሽ አባል ወ/ሮ አበባ ስፍታዬ በበኩላቸው ለም/ቤቶች ከቀረበው ሪፖርት መነሻ ምልከታ ባደረጉባቸው ወረዳዎች በከፊል መልካም ጅምሮችን መመልከታቸውን ጠቅሰው መታረም የሚገባቸው ነጥቦች አንስተዋል።
ለአብነትም የሴትና ወንድ ተጠርጣሪዎች ለይቶ ማቆያ በአብዛኛው ወረዳዎች ጥሩ ቢሆኑም በአንዳንዶቹ የሴት ማቆያ ያለመኖር መታዘባቸውን ገልጸዋል።
በዳሰነችና ቱርሚ ፖሊስ ጣቢያዎች ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህጻናት ሞግዚትን ጨምሮ የተለዬ የማቆያ ስፍራ መዘጋጀቱን አድንቀው፤ የቀበሌ ም/ቤቶችን ከማዋቀር አኳያ በአመዛኙ የተሻሉ ነገሮችን ቢመለከቱም ሊጠናከሩ ይገባልም ብለዋል።
የቋሚ ኮሚቴዎቹን ቡድን በመምራት በማህበራዊ ኢኮኖሚና በህግ ፍትህና መልካም አስተዳደር መስኮች ምልከታ እያደረጉ የሚገኙት የሽግግር ም/ቤቱ ም/አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ዶቦ እውኖ በፍትህ ዘርፉ የተጠርጣሪ አያያዝን ጨምሮ በ24 ሰዓት ለህግ የማቅረብ ስራዎችን በጥንካሬ ተመልክተዋቸዋል።
በአዳንድ የተጠርጣሪ ማቆያዎች ንጽህና መጓደል፤ የመጸዳጀና የሻወር አገልግሎት አለመኖር እንዲሁም በቂ ብርሃን የሌላቸው፤ በርና መስኮቶቻቸው ጥገና የሚሹ እንዳሉ በማንሳት እኝህም በአፋጣኝ እንዲታረሙ ግብረ መልስ ተሰጥቷልም።
ድንበር አካባቢ ሰላም ለማረጋገጥና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመግታት ብሎም በኢግዚቢትነት የተያዙ ንብረቶች በአግባቡ ለማስቀመጥ እየተደረጉ ጥረቶችም በመልካም ጎናቸው የሚጠቀሱ እንደሆኑ አብራርተዋል።
እንደ አዲስ መዋቅር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የፍትህ ስርአቱን ለማሻሻል፤ የዜጎችንም ሰብአዊ ክብር የሚያስጠብቁ በመሆናቸው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ዘጋቢ: ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
ክህሎት መር ስልጠና በመተግበር በሀገሪቱ ያለውን ፀጋ ተጠቅሞ በትጋት ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲሱን የገቢ ግብር አዋጅ መሰረት በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑ ተገለጸ
ታራሚዎች በስነ ምግባርና በሙያ ታንፀው ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የሳውላ ማረሚያ ተቋም አስታወቀ