ታራሚዎች በስነ ምግባርና በሙያ ታንፀው ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የሳውላ ማረሚያ ተቋም አስታወቀ
የሳውላ ማረሚያ ፖሊስ ተቋም አዛዥ ኮማንደር ብርቱካን መንግስቱ፤ ታራሚዎች በማረሚያ ቆይታቸው በስነ ምግባርና በሙያ ታንፀው ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ታራሚዎች በእንጨትና ብረታ ብረት፣ በብሎኬት ማምረት፣ በሽመና፣ በልብስ ስፌት እና በሌሎች የስራ መስኮች ተደራጅተው የሚያመርቱትን ምርት ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ እየተሰራ እንዳለም አስረድተዋል።
ታራሚዎች በተደራጁበት የስራ መስክ በመስራት የተሻለ ገቢ በማግኘት እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከመርዳት በተጨማሪ የዕርምት ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ የሙያ ባለቤት በመሆን ከኢኮኖሚ ችግር ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለመታደግ ያስችላል ብለዋል።
ኮማንደር ብርቱካን አክለውም ከመንግስት አካላት በተጨማሪ የሀይማኖት ተቋማትና ረጂ ድርጅቶች ማረሚያ ቤቱን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።
በተቋሙ የማረምና ማነፅ ተሀድሶ ልማት ዲቪዥን አስተባባሪ ረዳት ኢንስፔክተር ምስክር አበራ በበኩላቸው፤ ታራሚዎች በቴክኒክና ሙያ ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግና በማህበር በማደራጀት የመስሪያ ቦታ ተመቻችቶላቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የማረሚያ ቤቱን የማረምና ማነጽ ስርዓት ይበልጥ በማሻሻል ታራሚዎች በስነ ምግባርና ሙያ ታንፀው እንዲወጡ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ሲሉ ገልፀዋል።
የታራሚዎች ሰብአዊ መብት አያያዝ በየጊዜው ክትትል እየተደረገ መሻሻል እያሳየ እንደሚገኝና መደበኛ ትምህርትና የጤና አገልግሎት በአግባቡ እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ያነጋገርናቸው የህግ ታራሚዎች በሰጡት አስተያየት፤ በተቋሙ በተፈጠረላቸው የስራ እድል ተጠቃሚ በመሆን የእርምት ጊዜያቸውን አጠናቀው ከማህበረሰቡ ጋር በሚቀላቀሉበት ጊዜ በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ በመሰማራት ሰላማዊና አምራች ሀይል እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አስመልክቶ የተዘጋጀ የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው
የደቡብ ኦሞ ዞን ሽግግር ምክር ቤት የአስፈጻሚ ተቋማት አፈጻጸም ምልከታው በዳሰነች ወረዳ ቀጥሏል
በከተማው ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በቂ ባለመሆኑ መቸገራቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ