20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አስመልክቶ የተዘጋጀ የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው

20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አስመልክቶ የተዘጋጀ የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው

ሀዋሳ፣ ህዳር 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አስመልክቶ የተዘጋጀ የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

መድረኩ የተዘጋጀው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ሲሆን ፤ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ፤ ከፌደራል ጀምሮ በተዋቀሩ ኮሚቴዎች ደረጃ ቅድመ-ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ፌደራሊዝምን እና የሕገ-መንግስትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል።

20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ከወትሮ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎችን በፍጥነት ማከናወን ይገባል ብለዋል።

“ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ በሚከበረው በዚህ በዓል ላይ የክልሉን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ባህልና ወግ ለማሣየት ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በዓሉ በክልሉ በሚገኙ ዞኖች ደረጃ ሲከበር ወንድማማችነትን እና አብሮነትን በሚያጎላ መልኩ እንዲሆን አሳስበዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ ጌታቸው ኬኒ በዓሉ ባለፉት 19 ዓመታት በተለያዩ ክልሎች ሲከበር መቆየቱን አስታውሰዋል።

ዘንድሮ የሚከበረው በዓል በህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በሚያጠናክር ሁኔታ ማክበር እንዲቻል መድረኩ መሰናዳቱን ገልጸዋል።

በመድረኩ ዴሞክራሲ እና የፌደራል ስርዓት በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድ እየቀረበ ሲሆን ፤ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ ከቦንጋ ጣቢያችን