የደቡብ ኦሞ ዞን ሽግግር ምክር ቤት የአስፈጻሚ ተቋማት አፈጻጸም ምልከታው በዳሰነች ወረዳ ቀጥሏል

የደቡብ ኦሞ ዞን ሽግግር ምክር ቤት የአስፈጻሚ ተቋማት አፈጻጸም ምልከታው በዳሰነች ወረዳ ቀጥሏል

በወረዳው በተለያዩ ተቋማት በተደረገ ምልከታ በተስተዋሉ ውስንነቶችና ጠንካራ ጎኖች ላይ በቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ግብረ መልስም ተሰጥቷል።

በኦሞራቴ ጤና ጣቢያና አዳሪ ትምህርት ቤት፤ የፖሊስ ጣቢያው የታራሚ አያያዝን ጨምሮ የግብርና ስራዎች በትኩረት ምልከታ ከተደረገባቸው መካከል ይገኙበታል።

በግብርናው ዘርፍ ድንገተኛ አደጋ ጊዜ በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች በቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ የተፈተሸ ሲሆን በኦሞ ራቴ ከተማ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አስተዳደር ያለው ውስንነት መታረም እንደሚገባው ተመልክቷል።

ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተሰሩ ስራዎች ላይ ጉብኝት የተደረገ ሲሆን በድርቅ ወቅት በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት ማሽላ ከማምረት ባሻገር፤ 116 ኩንታል መጠባበቂያ እህል መቀመጡንም የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅረ ማሪያም አይመላ ማብራሪያ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ለዚሁ የአደጋ ጊዜ ምላሽ 50 ሄክታር መሬት ላይ ማሽላ ለማልማት ታቅዶ በ24 ሄክታር መሬት ላይ የማሽላ ሰብል ማልማት መቻሉንም አብራርተዋል።

ከተረጅነት ወደ ምርታማነት በመሸጋገሩ ተግባርም በወረዳ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ በመሆኑ በቋሚ ኮሚቴዎቹ በጠንካራ ጎን መገምገሙን በዞኑ ምክር ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢው አቶ ታደለ ወዝጋ ገልጸዋል።

የማሽላ ምርታማነትን በማሳደግ ለድንገተኛ የርሃብ አደጋ ምላሽ የመስጠቱ ጅምር ተግባር መልካም ቢሆንም በቂ ባለመሆኑ የማስፋት ስራ ሊሰራ እንንደሚገባም በቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ማሳሰቢያ መሰጠቱንም አብራርተዋል።

እንደ ወረዳ በተለይ መጠባበቂያ የምግብ ክምችት ለማኖር የተጀመረው ስራ አርብቶ አደሩን ከተረጂነት አስተሳሰብ የሚያላቅቅ እንደሆነ ያነሱት ምክትል ሰብሳቢው፤ ከተረጂነት ለመውጣት የሚያግዝ በመሆኑ ልምዱ ተቀምሮ መስፋት እንዳለበትም አስምረውበታል።

በሌላ በኩል በወረዳው ኦሞራቴ ከተማ ከ600 በላይ ተማሪዎች የሚያስተናግደው የከተማው አዳሪ ትምህርት ቤት ችግሮች በቋሚ ኮሚቴው ምልከታ ተደርጎበታል።

በሆስቴሉ በተማሪዎች አያያዝ፤ ውስጣዊ አደረጃጀትና አስፈላጊ ግብዓት ያልተሟሉለት በመሆኑ ከፍተኛ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ነው የወረዳው መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ጽ/ቤት ኃላፊው ወ/ሮ ማልድሬት ታረቀኝ የገለጹት።

የልበ ሙቀት አዳሪ ትምህርት ቤት በውሃ ሙላት ምክንያት መበተኑን ተከትሎ 298 ተማሪዎች እንዲገቡ መደረጉ ይበልጥ ችግሩን እንዳባባሰው ጠቅሰው፤ ከተማሪዎቹ ቁጥር አንጻር ተመጣጣኝ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉንም አብራርተዋል።

የምግብ አቅርቦት፣ የመኝታና የህክምና አገልግሎትም ችግርን ጨምሮ የተማሪዎች በጀት በአግባቡና በወቅቱ የሚደርስ ባለመሆኑ ተማሪዎች ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረጉ መሆናቸውን ነው ያብራሩት።

ወረዳው ከ8 መቶ ሺህ ብር በላይ በጀት በመመደብ የአዳሪ ት/ቤቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ሰፊ ጥረት ማድረጉና በቆላማና መስኖ አካባቢዎች ልማት መስክ የሚደረጉ ድጋፎች በጠንካራ ጎን በመጥቀስ ተቋሙ ካሉ ችግሮች ስፋት አንጻር በቂ አለመሆኑን ምክትል ሰብሳቢው አመላክተዋል።

የተወሳሰበ ችግር ያለበት አዳሪ ት/ቤቱ የተሻሉ ተማሪዎችን ማፍራት የሚጠበቅበት መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደ ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ የተነሱበት ችግሮች እንዲፈቱ ለሚመለከታቸው አካላት ግብረ መልስ ይሰጥበታል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምልከታ በሐመር፣ በና ጸማይ፣ ሳላማጎና ማሌ ወረዳዎች እንደሚቀጥል ተመላክቷል።

ዘጋቢ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን