የጎርደና ሴራ አካል የሆነው የኦማኖ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት የህብረተሰቡን ችግር በመፍታትና በማቀራረብ ለመንግስታዊው የፍትህ ስርዓት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የኦማኖ ስርዓት በማህበረሰቡ ዘንድ ለሚፈጠሩ ግጭቶች እርቅን በማውረድ ትልቅ አበርክቶ እየሰጠ እንደሚገኝ በምስራቅ ጉራጌ ዞን የደቡብ ሶዶ ወረዳ አካባቢ ሽማግሌዎች ገልጸዋል።
አቶ ነጋሽ ሞላ፣ አቶ ደርሰ ወልደሰንበት እና አቶ ደምሴ ከበደ በኦማኖ ስርዓት መሰረት በሰዎች መካከል የተፈጠሩ ዘርፈ ብዙ ይዘት ያላቸው ጉዳዮችን በማየት የእርቅና የካሳ ብይን የሚሰጡ አባቶች እንዳሉት፤ ኦማኖ በሶዶ ክስታኔ ቤ-ጉራጌ ዘንድ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለሚፈጠሩ ግጭቶች እርቅን በማውረድ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
ሥርዓቱ ተደብቀው የቆዩ የደምና ሌሎች ግፎች በፈጣሪ ፊት ግልጽ በማድረግ የይቅርታ ምሪት የሚሰጥበት ስለመሆኑም ሽማግሌዎቹ ተናግረዋል።
በኦማኖ ከሚታዩ ጉዳዮች መካካል ቀዳሚው የሰው ህይወት ማጥፋት ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ይህም የግፍ አገዳደል፣ የግፍ ግፍ አገዳደል፣ የአልሞት ባይ ተጋዳይ እና (የሳቻ) የስህተት ተብሎ እንደጥፋቱ የደም ካሳ ውሳኔ በመስጠት እርቅ እንደሚወርድ አስረድተዋል።
በአካባቢው ከኦማኖ ስርዓት በላይ የሆነ ጉዳይ የለም ያሉት አባቶቹ፤ የሰው አካል ማጉደል፣ የእንስሳት ህይወት ማጥፈትና አካል ማጉደል፣ የተደበቁ ግፎች ማውጣት፣ የመሬት ይዞታ ይገባኛልና የንብረት ግጭት፣ የተለያዩ የእምነት መካካዶች ተመርምረው ሁለቱም ወገን በሚያግባባ መልኩ በፍትሀዊነት ይፈቱበታል ብለዋል።
ማህበረሰቡ በፍርድ ቤት ሲያከራክሩ የቆዩ የክስ አለመግባባቶች መልሶ ወደ ኦማኖ በማምጣት እልባት እንደሚያገኝ በመጥቀስ፤ ከአካባቢው ተወላጆች ባሻገር ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ሰዎችም አገልግሎቱን እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ለመንግስታዊው የፍትህ ስርዓት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ በመሆኑ ከተገልጋዩ ቁጥር አንጻር መጠለያና የውሳኔዎች ህጋዊነት ማረጋገጫ ማህተም እንዲሟላላቸው ጠይቀዋል።
በምስራቅ ጉራጌ ዞን የደቡብ ሶዶ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እስከዳር ሲሳይ የኦማኖ የግጭት አፈታት ስርዓት የጎርደና ሴራ አካል ሆኖ ከ900 ዓመት በፊት የሶዶ ክስታኔ ቤተ ጉራጌ ማህበረሰብ ሲገለገልበት የመጣ ነባር ባህላዊ ስርዓት መሆኑን ገልጸዋል።
የኦማኖ ስርዓት በግጭት አፈታት ለፍትህ ተቋማት አስቸጋሪ የሆኑ የማህበረሰቡ ችግሮችን መርምሮ በማየትና በማቀራረብ ለመንግስታዊው የፍትህ ዘርፍ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን አውስተዋል።
አገልግሎቱ በደቡብ ሶዶ ወረዳ ኬላ ከተማ በወር ሁለት ጊዜ እንደሚሰጥ የተናገሩት ኃላፊዋ፤ ይህን ባህላዊ እሴት ትውልዱ ከአባቶቹ ተቀብሎ ሊያስቀጥለው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኦማኖ አባቶች እንዲሟላ ያነሱት አገልግሎት የሚሰጡበት መጠለያ ቦታ መረከባቸውንና ማህበረሰቡንም በማስተባበር ቢሮ ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልፀው፤ የህጋዊነት ማረጋገጫ ማህተም ችግርም በአጭር ጊዜ እንደሚፈታም ተናግረዋል።
በምስራቅ ጉራጌ ዞን የደቡብ ሶዶ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የባህልና ታሪክ ጥናት ቅርስ ጥበቃ ባለሙያ አቶ ይስሀቅ ለማ በበኩላቸው፤ የኦማኖ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ከዘመናዊው የፍትህ ስርዓት ባልተናነሰ መልኩ በማህበረሰቡ መካከል የሚፈጠሩ የተለያዩ ችግሮችና የደም ጉዳዮች በአግባቡ እየተፈቱበት ነው ብለዋል።
ይህንን አገልግሎት ለማግኘት ከተለያዩ አካባቢዎች እንግዶች ይመጣሉ ያሉት ባለሙያው፤ እንደ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ተቋም በስርዓቱ አፈጻጸም ላይ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ትውፊት ወደ ቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ መንግስት እና ተገልጋዩ ማህበረሰብ በቅርበት መደገፍ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡ አዱኛ ትዕዛዙ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የክህሎት ዘርፍ የልማት ሞተር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር መሰረትና የስራ ፈጠራ ዋንኛ ምንጭ መሆኑ ተገለፀ
የአንታሊያው ኮፕ 31 ጉባኤ የመጨረሻ ቀኑ ላይ ይገኛል
የመሬት ሀብትን ወደ ካዳስተር ሲስተም አስገብቶ ሀብት በማመንጨት ለአካባቢው ልማት ማዋል እንደሚገባ ተገለፀ