‎የመሬት ሀብትን ወደ ካዳስተር ሲስተም አስገብቶ ሀብት በማመንጨት ለአካባቢው ልማት ማዋል እንደሚገባ ተገለፀ

‎የመሬት ሀብትን ወደ ካዳስተር ሲስተም አስገብቶ ሀብት በማመንጨት ለአካባቢው ልማት ማዋል እንደሚገባ ተገለፀ

‎

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሬት አስተዳደር ቢሮ የድጋፋዊ ክትትል ቡድን በቡርጂ ዞን በመገኘት የመቶ ቀን ዕቅድ አተገባበር ግምገማ አካሂዷል።

‎

‎የመሬት ሀብትን በከተማ አስተዳደር ደረጃ ወደ ዘመናዊ የካዳስተር ሥርዓት በማስገባት ከተሞች ማግኘት የሚገባቸውን ሀብት በማመንጨት ለልማት እንዲያውሉ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑ ተመላክቷል።

‎‎የቡርጂ ዞን የመሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አኖ እንደገለፁት፤ ከክልሉ የመሬት አስተዳደር ቢሮ ከመጡ አካላት ጋር የመቶ ቀን ዕቅድ ትግበራ መገምገሙን ጠቁመው፤ መሬትን ለክቶ ወደ ዘመናዊ አስተዳደር ሥርዓት ከማስገባት አኳያ ‎በሶያማ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር የተሻለ አፈፃፀም መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በሶያማ ከተማ አስተዳደር ደረጃ በተለያዩ ምክንያቶች መሬት ተለክቶ ወደ ካዳስተር ሥርዓት ማስገባት አለመሉቻን አመላክተዋል።

ኃላፊው አያይዘውም በዞኑ የቢፒአር(BPR) አተገባበር ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መግባቱን ገልፀው፤ በጥናቱ መሰረት የሰው ኃይል ቢመደብም በበጀት እጥረት ምክንያት አሁንም ከሚፈልገው አኳያ በቂ ባለመሆኑ አስፈላጊውን ሥምሪት መሥጠት አልተቻለም ብለዋል።

‎

በክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ የማረጋገጥ ባለሙያ ‎‎አቶ ተመስገን ጎርክሳ በበኩላቸው፤ የBPR መደብ ትግበራ፣ ህገወጥ ይዞታዎችን ለክቶ ወደ ህጋዊነት ከማስገባት አኳያ በዞኑ የተሻለ ሥራ መሠራቱን በመቶ ቀን ዕቅድ አተገባበር ግምገማ ወቅት መመልከታቸውን አስረድተዋል።

‎

‎በወረዳው በሚገኙ የገጠር አከባቢዎች እየተሠሩ ያሉ የመሬት ልኬት ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በከተሞች አከባቢ አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ግብዓት እጥረት ምክንያት የከተማ መሬትን ወደ ካዳስተር ማስገባት እንዳልተቻለ መረዳታቸውን ገልፀዋል፡፡

‎በመድረኩ የመሬት ሀብት በአግባቡ ለክቶ ወደ ካዳስተር ሥርዓት ማስገባት ከተሞችን ወደ ዘመናዊ አሠራር ከማምራት ባለፈ ከመሬት ሊገኝ የሚገባውን ሀብት ለከተሞች ልማት ማዋል ስለሚያስችል በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ መተግበር እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።

‎

የዞኑ የመሬት አስተዳደርና የሶያማ ከተማ አስተዳደር የመሬት ዩኒት ባለሙ የሆኑት ‎አቶ ሽቢያ ሀይሉ እና አቤል ሹኮ እንደተናገሩት፤ በግምገማው በመቶ ቀን ዕቅድ በተሠሩ ሥራዎች እና ጉድለቶች ላይ ተነጋግረው መግባባታቸውን ጠቁመው፤ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችና ቀጣይ ሊሠሩ በሚገቡ ተግባራት ዙሪያ በትኩረት እንደሚሠሩ አንስተዋል።

‎

‎በተለይም በከተማ አከባቢ መሬትን ለክቶ ወደ ካዳስተር ሥርዓት ከማስገባት አኳያ የድጋፍ እና ክትትል ባለሙያዎች በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ቃል መግባታቸው ለቀጣይ ሥራ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ከዚህ ቀደም ህገወጥ ተብለው የነበሩ ይዞታዎችን ወደ ህጋዊ መንገድ ለማስገባት የተሰራው ሥራ እንደ ጠንካራ ጎን መነሳቱን በሰጡት አስታያየት አንስተዋል።

‎

‎ዘጋቢ፡ አብዶ አየለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን