የአንታሊያው ኮፕ 31 ጉባኤ የመጨረሻ ቀኑ ላይ ይገኛል
ቱርክዬ በአንታሊያው የኮፕ 31 ጉባኤ ደምቃ ይኸው እንግዶቿን ከዛሬ በኋላ ልትሸኝ ተሰናድታለች፡፡ ላለፉት 10 ቀናት የተካሄደው ጉባኤውም የመጨረሻ ቀን ውሎውን ያደርግና ይቋጫል፡፡
በጉባኤው የተለየ የሚባል አዲስ ነገር ባይኖርም ከየትኛውም ጊዜ በላይ መንግስታት ግፊት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ድርድርም ተደርጓል፡፡ በይበልጥ የተሰማው ድምጽ ግን ተግባራዊነት፣ ተግባራዊነት… ተግባራዊነት የሚል ነው፡፡
ይህ ዓለም ምን ያህል ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚያ ላይ ለውጡን ለመከላከል ስምምነቶችን ተግባራዊ ማድረግ ላይ የኃያላን ሀገራት ምላሽ እምብዛም መሆኑ በቁርጠኝነት ለመስራት የተነሱ መንግስታትን ማበሳጨቱ አልቀረም፡፡
አሁን መሬት ላይ ያለው ሃቅ ግን ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፡፡ የአየር ንብረት ለውጡ የዓለም ማህበረሰቡን ክፉኛ እየጎዳ ነው፡፡ በአንታሊያው ጉባኤ ወቅትም የተወሳው ዓለምን ያስጨነቀው ይኸው ጉዳይ ነው፡፡
የዓለም ሚቴዎሮሎጂ ተቋም (WMO) በሪፖርቱ እንዳመላከተው፤ ከአውሮፓዊያኑ ከጥር እስከ መስከረም 2026 ባሉት ወራት ውስጥ የዓለም አማካይ የሙቀት መጠን ከቅድመ ኢንደስትሪ ዘመን ደረጃ በ1.47 ድግሪ ሴልሺየስ ገደማ ጨምሯል፡፡
ይህም ማለት ከኢንደስትሪ በካይ ጋዝ ወደ ከባቢ መልቀቅ ከመጀመሩ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በፊት ከነበረው የሙቀት መጠን በአሁኑ ወቅት 1.47 ድግሪ ሴልሺየስ ከፍ ብሏል፡፡ የዓለም የባህር ጠለል ከፍታም በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ጨምሯል፡፡
በዚህም ምክንያት በሙቀት መጨመር ሳቢያ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችና የሰዎች የጤና እክል ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
ይህን ተከትሎም በአንታሊያ ጉባኤው ከመክፈቻው ቀን ጀምሮ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ የተነሳው የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ የንጹህ ኃይል ሽግግር (Clean Energy Transition) እና ለታዳጊ ሀገራት የሚደረግ የጉዳት ካሳ ድጋፍ ናቸው፡፡
አጀንዳዎቹን መነሻ በማድረግ አውስትራሊያ ድርድሮችን የመምራት ኃላፊነት ወስዳ ስታደራድር ቆይታለች፡፡
የገንዘብ ድጋፍን በተመለከተ በተነሳው አጀንዳ በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱና ተጋላጭ ለሆኑ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የበለጸጉ ሀገራት የሚያቀርቡትን የገንዘብ ድጋፍ ማሳደግ ዋና ዒላማ ተደርጎ ተነስቷል፡፡
ይሁን እንጂ አከራካሪ ነገር መነሳቱ አልቀረም፡፡ በድርድሩ ወቅት የተነሳው ክርክር ማነው የድጋፍ ገንዘብ መክፈል ያለበት? የሚከፈለው የገንዘብ መጠንስ ስንት መሆን አለበት? የሚለው ነው፡፡
ሌላው በአጀንዳነት የተነሳው የንጹህ ኃይል ሽግግር ሲሆን እስከ 2035 ድረስ የዓለም የኃይል አጠቃቀም 35 በመቶ በኤሌክትሪክ እንዲሸፈን የሚያበረታታ የበጎ ፈቃድ ግብ ለመቅረጽ ውይይት ተደርጓል፡፡
ከዚሁ በተጓዳኝ የቅሪተ አካል ነዳጅ ተብለው ከሚጠሩት ከድንጋይ ከሰል፣ ከነዳጅና ከተፈጥሮ ጋዝ ጥገኝነት ለመውጣት በሚወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያ በሀገራት መካከል አሁንም ልዩነቶች መኖራቸውንና ልዩነቶችን ማጥበብ ላይ ድርድር መደረጉንም ቲአርቲ በዘገባው አስፍሯል፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን በሌላኛው አጀንዳነት የተነሳው በአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ የሆኑት የአፍሪካ ሀገራትን የመሳሰሉት የድርቅ መቋቋም አቅምን መገንባት፣ የግብርና ልማት፣ የውሃ ደህንነት እና ለንጹህ ኃይል ፕሮጀክቶች የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ላይም ድርድር ተደርጓል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በድርድሩ ፍትሃዊ ውጤት እንዲመጣ አንድነታቸውን አጠናክረው እየተከራከሩ ስለመሆናቸው ተወስቷል፡፡
ኢትዮጵያም በቀጣዩ ዓመት በአዲስ አበባ ለምታስተናግደው ኮፕ 32 ጉባኤ የልምድ ልውውጥና የዲፕሎማሲ ሥራዎችን እየሰራች ትገኛለች፡፡
ዘጋቢ፡- ኢያሱ ታዴዎስ

More Stories
የክህሎት ዘርፍ የልማት ሞተር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር መሰረትና የስራ ፈጠራ ዋንኛ ምንጭ መሆኑ ተገለፀ
የጎርደና ሴራ አካል የሆነው የኦማኖ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ለመንግስታዊው የፍትህ ስርዓት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑ ተገለፀ
የመሬት ሀብትን ወደ ካዳስተር ሲስተም አስገብቶ ሀብት በማመንጨት ለአካባቢው ልማት ማዋል እንደሚገባ ተገለፀ