‎በከተማው ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በቂ ባለመሆኑ መቸገራቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

‎በከተማው ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በቂ ባለመሆኑ መቸገራቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

‎‎የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ውሃ አገልግሎት በበኩሉ በከተማው ያለውን የውሃ ችግር ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

‎ወ/ሮ አበበች ሽብሩ፣ አቶ ታደለ አበበ እና ሌሎችም የከተማዋ ነዋሪዎች፥ ይርጋጨፌ ውሃማ አካባቢ እንደሆነች የሚታወቅ ቢሆንም በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት መቸገራቸውን ነው የሚገልጹት።

‎በከተማው ላይ የውሃ አቅርቦት በቂ ካለመሆኑ የተነሳ ንፁህ ያልሆነ የምንጭ ውሃ ለመጠቀም እንደሚገደዱና ለተለያዩ የውሃ ወለድ በሽታዎች እንደሚዳርጋቸውም ተናግረዋል።

‎የሚመለከታቸው አካላት ህብረተሰቡን በማስተባበር ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚዎች እንዲያደርጓቸው በመሥራት ችግሩን እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

‎የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ውሃ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ታሪኩ፤ በከተማዋ ያለው የውሃ ሽፋን ዝቅተኛ ወይም 15 በመቶ ብቻ እንደሆነ ጠቁመው ህብረተሰቡ የሚያነሳው ቅሬታ ትክክል እንደሆነ ገልጸዋል።

‎ከጊዜ ወደጊዜ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ ከአገልግሎት ብዛት የተነሳ የውሃ ፓምፖች ብልሽት፣ የመብራት መቆራረጥና ኃይል ማነስ በዋናነት በከተማዋ ላለው የውሃ ችግር በምክንያትነት አንስተዋል።

‎ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እየሠሩ እንዳሉ በመግለፅ ህብረተሰቡም የድርሻውን መወጣትና ማገዝ አለበት ብለዋል።

‎ዘጋቢ: ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን