በግሉ የኢንቨስትመንት ልማት ዘርፍ እየታዬ ያለውን መነቃቃት ይበልጥ ለማጎልበት ከመንግስት በኩል የሚጠበቁ ድጋፎች መጠናከር እንዳለባቸው የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት አሳሰበ
ሀዋሳ፣ ሕዳር 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በግሉ የኢንቨስትመንት ልማት ዘርፍ እየታዬ ያለውን መነቃቃት ይበልጥ ለማጎልበት ከመንግስት በኩል የሚጠበቁ ድጋፎች መጠናከር እንዳለባቸው የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት አሳሰበ።
በዞኑ ሽግግር ም/ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ የተመራ የቋሚ ኮሚቴዎች ቡድን በኛንጋቶም ወረዳ የምስክር ኃ/ኢየሱስ የግብርና ኢንቨስትመንት የልማት ስራዎችን ጎብኝቷል።
የልኡካን ቡድኑ በወረዳው የግል ኢንቨስትመንት ተቋማት ስራዎች ላይ ምልከታ ያደረገ ሲሆን በምስክር ኃ/ኢየሱስ የግብርና ኢንቨስትመንት ልማት እየለማ የሚገኝውን የፍራፍሬና የሰብል ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በ150 ሄክታር መሬት ላይ ሙዝ፣ የፓፓያ፣ ሀብሀብን ጨምሮ የበርበሬ፣ ሩዝና፣ ማሾ፣ ለውዝና በርበሬ እንዲሁም ንብ የማነብ ስራዎች በአካባቢው አግሮ ኢኮሎጂ ውጤታማ መሆናቸውን በመጥቀስ ለቀጣይ እስከ 300 ሄክታር መሬት ለማልማት ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ በመንግስት በኩል ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግላቸው የአልሚ ባለሃብቱ ተወካይ አቶ ታጠቅ ኃይሉ ገልጸዋል።
በካንጋቴን ከተማ ነዋሪ የሆኑት ግለሰቡ በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆን በጀመሩት የግብርና ስራ ውጤታማ ከመሆን ባለፈ ከ90 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል በፈጠረው ተቋም በሙሉ አቅም ወደ ስራ መግባት ከተቻለ በሺዎች ለሚቆጠሩ ተጨማሪ ዜጎች የስራ እድል አማራጭ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
የሚመረቱት የፍራፍሬ ምርቶች ቶሎ የሚበላሹ በመሆናቸውም የገበያ ትስስር ለመፍጠር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ያሳሰቡ ሲሆን በፓምፕ ለሚያለሙት የግብርና ልማት ፈተና እየሆነ የሚገኘውን የነዳጅ ችግር ለመቅረፍም በአቅራቢያ ካለው የኤሌክትሪክ መስመር ኃይል እንዲዘረጋላቸውም ጠይቀዋል።
ከ49 በላይ የኢንቨስትመንት ተቋማት በሚገኙበት የኛንጋቶም ወረዳ በርካቶቹ ወደስራ ቢገቡም ወደ ስራ ሳይገቡ በቆዩት ላይ እርምጃ በመውሰድ የያዙትን መሬት ወደ መሬት ባንክ የመመለስ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የወረዳው አስተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ ዮሴፍ ኤካሌ ናቸው።
የደቡብ ኦሞ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ም/አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ዶቦ አውኖ እንደ ዞን የግል የኢንቨስትመንት ተቋማት ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ ምርት እስከ ማቅረብ የደረሱበት ሁኔታ መኖሩን አንስተዋል።
በምስክር ኃ/ኢየሱስ የግብርና ኢንቨስትመንት እየተሰሩ ባሉ የምርታማነት ስራዎችም ደስተኛ መሆናቸውን የጠቀሱት ም/አፈ ጉባኤዋ መሰል አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም ስኬታማ ይሆኑ ዘንድ በዞኑ በኩል ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም በኢንቨስትመንቱ በኩል ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ባሻገር አስፈላጊ የድጋፍ ስራዎችን በተሻለ መልኩ ለማቅረብ እንደሚሰራም ነው ያስገነዘቡት።
በመስክ ምልከታው የተገኙት ቋሚ ኮሚቴ አባላትም ከተወካዩ ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን በቀጣይ በተለይም ለአካባቢው አርብቶ አደሮች የስራ እድል በመፍጠር ብሎም ቴክኖሎጂ በማሻገር ረገድ የተጀመሩ ስራዎች በተሻለ መልኩ ሊከወኑ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ዘጋቢ፡- ወንድሜነህ አድማሱ ከጂንካ ቅርንጫፍ ጣቢያ

More Stories
የትራፊክ አደጋን መከላከል የማህበረሰቡ የሁል ጊዜ ተግባር መሆን እንደሚገባ ተገለፀ
በሴቶች ላይ የጡትና የማህፀን በር ካንሰር የሚያስከትለውን ሞት ለመቀነስ የካንሰር ቅድመ ምርመራ መደረግና ህክምና መውሰድ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የወጣቱን የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት በሥራ ዕድል ፈጠራ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥር ቀረበ