የትራፊክ አደጋን መከላከል የማህበረሰቡ የሁል ጊዜ ተግባር መሆን እንደሚገባ ተገለፀ

የትራፊክ አደጋን መከላከል የማህበረሰቡ የሁል ጊዜ ተግባር መሆን እንደሚገባ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) መተኪያ የሌለውን የሰው ህይወት እየቀጠፈ ያለውን የትራፊክ አደጋ መከላከል የማህበረሰቡ የሁል ጊዜ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ የጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት አስታወቀ።

የጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ከፖሊስ ጽ/ቤት ጋር በመሆን በወረዳው ሎጤ ክላስተር ”ፍጥነት ገዳይ ነው፤ አስተውለው ያሽከርክሩ” በሚል መሪ ቃል ለአሽከርካሪዎች እና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተዋል።

የደምባ ጎፋ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን አባይነህ የትራፊክ አደጋ መተኪያ የሌለውን የሰው ህይወት እየቀጠፈ በመሆኑ አደጋውን ለመከላከል የሚደረገው ርብርብ የሁሉም ሰው ተግባር መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል ።

የወረዳው አስተዳደር ከቁጥጥርና ክትትል ስራዎች ባሻገር ግንዛቤ ላይ መስራት ወሳኝ ጉዳይ አድርጎ እየሰራ መሆኑን አክለው ገልፀዋል።

የደምባ ጎፋ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ፖሊስ አዛዥ ተወካይ ዋና ሳጅን ያዕቆብ ካሳሁን የትራፊክ አደጋ መድኃኒት የሌለው ገዳይ በመሆኑ እግረኞች ግራቸውን ይዘው አለመጓዝ፣ አሽከርካሪዎች ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠት ፣ ጠጥተው ማሽከርከር እና የትራፊክ ህጎችን አለማክበር በስፋት የሚስተዋል በመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መስራት ማስፈለጉን ተናግረዋል።

አቶ አስራት አረጋ የደምባ ጎፋ ወረዳ መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት በመንገድ ደህንነት ትራፊክ ማረጋገጫ ዋና ስራ ሂዴት አስተባባሪ በወረዳው በ2018 በጀት ዓመት በትራፊክ አደጋ አንድ ሰው መሞቱን እና ንብረት መውደሙን ገልጸዋል።

የወረዳው ፖሊስ ጽህፌት ቤት የመንገድ ትራፊክ አደጋ ፍሰት ቁጥጥር ማስተባበሪያ ኃላፊ ተወካይ ረዳት ኢንስፔክተር ደሳለች ቦረና እንደገለፁት የትራፊክ አደጋ አብዛኛውን ጊዜ ሴቶችና ህፃናት ላይ የሚያስከትለው አደጋ ከፍተኛ መሆኑን አብራርተው አሽከርካሪዎች ከተፈቀደው ፍጥነት ወሰን በላይ ከማሽከርከር እንድቆጠቡ አሳስበዋል ።

የአይሱዙ መኪና አሽከርካሪ የአብስራ ከፍያለው ፣ የህዝብ ማመላለሻ መኪና አሽከርካሪ ወጣት ሙስጠፋ ሙህዲን እንደተናገሩት አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህጎችን አለማክበር ለአደጋዎች ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰው በግንዛቤ ስልጠናው ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል።

ትርፍ መጫንና በፍጥነት ማሽከርከር ጉዳቱ ለራስ መሆኑን ከአከባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ጌታሁን ዝግለ ፣ አቶ ስሜ ፍርዴ እና ወይዘሮ አልማዝ በቀለ በተሰጠው ግንዛቤ ትምህርቱ መሰረት አደጋውን ለመቀነስ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ኢያሱ አዲሱ – ከሳውላ ጣቢያችን