የወጣቱን የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት በሥራ ዕድል ፈጠራ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥር ቀረበ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወጣቱን የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት በሥራ ዕድል ፈጠራ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የጌዴኦ ዞን ሥራና ክህሎት መምሪያ አሳሰበ፡፡
መምሪያው የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት የ2018 1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ 90 ቀናት ዕቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
በሥራ ዕድል ፈጠራ ዕድል አግኝተው ሥራ የጀመሩ ወጣቶች ክህሎታቸውን፣ እውቀታቸውንና አቅማቸውን አሟጠው በመጠቀም ከዕለት ጉርሳቸው ባለፈ ለሌሎች ሥራ ፈላጊዎች ለመትረፍ በትጋት ሊሠሩ እንደሚገባ በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪና ሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል፡፡
በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ምክር ቤቱ፣ ተቋማት እና የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው አስተዳደሪው አሳስበዋል።
በዞኑ ያልተነካ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ፀጋ መኖሩን የገለጹት አስተዳዳሪዉ ሥራን እና ሥራ ፈላጊ ዜጎችን በማቀራረብ በኩል ብዙ መሥራት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የዞኑ የሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደለ ጥላሁን በዞኑ ያለውን እምቅ ፀጋ በመጠቀም ወጣቱ በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማ እንዲሆን ከሙያና ቴክኒክ ኮሌጆችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው ስልጠና በመስጠት ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ አፈፃፀም በብድር ስርጭትና አመላለስ የተስተዋሉ ችግሮችን በማረም በቀጣይ ለተሻለ ውጤት መምሪያው አፅንኦት ሰጥቶ እንደሚሠራም በውይይቱ አስገንዝበዋል፡፡
የወጣቱን የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት በስራ ዕድል ፈጠራ የሚከናወነው ተግባር ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አቶ ታደለ አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ የዞን አመራሮች ፣ የወረዳና ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት እየተሳተፉ ናቸው።
ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
በግሉ የኢንቨስትመንት ልማት ዘርፍ እየታዬ ያለውን መነቃቃት ይበልጥ ለማጎልበት ከመንግስት በኩል የሚጠበቁ ድጋፎች መጠናከር እንዳለባቸው የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት አሳሰበ
የትራፊክ አደጋን መከላከል የማህበረሰቡ የሁል ጊዜ ተግባር መሆን እንደሚገባ ተገለፀ
በሴቶች ላይ የጡትና የማህፀን በር ካንሰር የሚያስከትለውን ሞት ለመቀነስ የካንሰር ቅድመ ምርመራ መደረግና ህክምና መውሰድ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ