የሐይማኖት ተቋማት በአገር አንድነት፣ ሰላም ማስፈንና ግጭት አፈታት ሂደት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተገለጸ

የሐይማኖት ተቋማት በአገር አንድነት፣ ሰላም ማስፈንና ግጭት አፈታት ሂደት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተገለጸ

‎ሀዋሳ፡ ሕዳር 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሐይማኖት ተቋማት በአገር አንድነት፣ ሰላም ማስፈንና ግጭት አፈታት ሂደት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
‎
‎ዋና አስተዳዳሪው ግጭትን በሰላም ወደሚፈታባት እና የብሔር ብሔረሰቦች መገኛ ወደሆነችው ለምለሚቷ ከተማ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
‎
‎ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር)፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአንድነት የምትታወቅ ሲሆን ይህንን አንድነት በማጠናከር ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።
‎
የሰው ልጅ ለሰላም ፍለጋ ወደ ፈጣሪና ወደ ሃይማኖት ተቋማት የሚመለከት በመሆኑ አመጽና ክፋትን ለመዋጋትም ጭምር ተቋማቱ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚጫወቱ አጽንኦት ሰጥተዋል።
‎
‎አክለውም፤ በክልላቸውና በአገሪቷ በዘላቂነት መለወጥ የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ መሆኑን በመጥቀስ ማህበራዊ ትስስርንና ሀገረ መንግሥትን በሰላም ግንባታ ለማጠናከር የሃይማኖት ተቋማት ሚና እጅግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
‎
‎የጋሞ ዞን አስተዳደር የሃይማኖት ተቋማት ተቻችለውና ለሰላም ዘብ መቆም እንዲችሉ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።
‎
‎የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር)፤ የሰላምን አስፈላጊነት እና ከተማዋ ለሰላም እያደረገች ያለችውን ጥረት አብራርተው ጉባኤውን ለማስተናገድ ዕድል በማግኘታቸው እንደተደሰቱ ገልጸዋል።
‎
‎ኢትዮጵያ በአንድነቷ የምትታወቅ ብትሆንም “በክፉ ሀሳብ በቆሙት” በመፈተን ላይ እንደቆየች እና ሀገሪቱ ያለውን አቅም እንዳትጠቀም መደረጓን አስታውሰዋል፤ ቀደምት አባቶች እንቅፋቶችን እንዳለፉ ሁሉ ዛሬም ትውልዱ የሰላም ችግሮችን የመፍታት ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።
‎
‎በሰላም እጦት ምክንያት በሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደደረሱ አመልክተዋል።

ሆኖም ከተማዋ ሁለንተናዊ የሰላም ንፋስ እንዲነፍስ እያደረገች እንደምትገኝ እና አመርቂ ውጤትም በማስመዝገብ ላይ እንዳለች አብራርተዋል።
‎
‎አርባ ምንጭ “በእርጥብ ሳር ጠብን ያበረዱበት ስፍራ” መሆኗን በመጥቀስ የሰላም ምልክት መሆኗን ተናግረዋል።

የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።
‎
‎ይህ 5ኛው ሀገር አቀፍ ጉባኤ ተቀራርቦ ስለሰላም አብሮ ለመስራት እንዲሁም የሀገሪቱን ቱባ ባህሎችና ህብረብሔራዊነትን ለማጎልበት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አጽንኦት ሰጥተዋል።
‎
‎በመሆኑም ወደ ከተማዋ የመጡ እንግዶች የከተማዋን ተስፋ ሰጪ ልማትና ተፈጥሮ ሀብቶች እንዲሁም ድንቅ ባህሏን እንዲመለከቱና ሰላማዊ ቆይታ እንዲያደርጉ ምኞታቸውን ገልጸዋል።
‎
‎ዘጋቢ፡ አማሮ አርሳባ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን