በተከናወነው የተቀናጀ ተግባር የወባ በሽታ ስርጭት እየቀነሰ መምጣቱን በዳዉሮ ዞን የታርጫ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ

በመከላከል ሥራ ላይ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ እየጎለበተ መምጣቱ ለወባ በሽታ ስርጭት መቀነስ የድርሻውን እያበረከተ እንደሆነም የዳዉሮ ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል።

ባለፉት ዓመታት የወባ በሽታ ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የዳዉሮ ዞን ቆላማ አካባቢዎች ተጠቃሾች ናቸው።

ይሁን እንጂ በተደረገው የወባ በሽታ የማከምና የመከላከል ሥራዎች ግን ከአምናው ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በጤና ተቋማት የተኝቶ ታካሚዎችና የሟች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን መረጃዎች ያሳያሉ።

በዞኑ፣ ታርጫ ዙሪያ ወረዳ የጎዞ ሻሾ ቀበሌ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ ተማሪዎችን ከትምህርታቸው፣ አርሶአደሮችን ከማሣ ሥራቸው አስተጓጉሏል።

አሁን ላይ ግን በተከታታይነት በተከናወነው የአካባቢ ቁጥጥር ሥራና በዳበረው የአጎበር አጠቃቀም ልማድ እንዲሁም በተገቢው የመድኃኒት አወሳሰድ ሥርዓት በማሣደግ ስርጭቱ በእጅጉን ቀንሷል ብለዋል።

በቀበሌው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ወይዘሮ ታደለች ተፈራ እንደተናገረችው ከደረሰው አስደንጋጭ ክስተት በመነሣት የተቀናጀ ሥራ ተሠርቷል።

ውጤቱም አሁን ላይ ተስፋ ሰጪ ሲሆን በበጀት ዓመቱም ይህንን ተግባር ለማጠናከር ይቻል ዘንድ ከ1 ሺህ 3 መቶ በላይ ለሚሆኑ አባወራዎች ከ2 ሺህ 5 መቶ በላይ አጎበር እየተሠራጨ እንደሆነም ነው የገለጸችው።

የዳዉሮ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ያዕቆብ ሌንጮ በበኩላቸው የወባ በሽታ መከላከልን መሠረት በማድረግ ለፈውስ ሕክምናም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንዳለም ነው ያብራሩት።

በተለይም በበጀት ዓመቱ በከጪና ታርጫ ዙሪያ ወረዳዎች የአጎበር ስርጭት እየተደረገ ሲሆን በገና እና ዲሳ ወረዳዎች ባለፈው ዓመት የተደረገው የአጎበር ስርጭት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተጨማሪ የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት እየተከናወነ እንዳለም ገልጸው ከመከላከሉ ስራ ባለፈ የግብዓት አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱንም አስረድተዋል።

በዞኑ በመከላከል ሥራ ላይ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ እየጎለበተ መምጣቱ ለወባ በሽታ ስርጭት መቀነስ የድርሻውን እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተው በቀጣይም በዜጎች ጤና ማስጠበቂያ ፓኬጅ ላይ በትኩረት እንደሚሠራም የመምሪያው ኃላፊ ተናግረዋል።

በዚህ ወቅት የወባ በሽታ የኅብረተሰቡ የጤና ችግር እስከማይሆንበት ደረጃ  ለማድረስ ኅብረተሰቡ በመከላከል ሥራ ተጠናክሮ መሳተፍ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- መሣይ   መሰለ   ከዋካ   ቅርንጫፍ