ከሪፖርት ባለፈ በተጨባጭ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ላይ ወቅታዊ የድጋፍና ክትትል ስራ አጠናክሮ መቀጠሉን የደቡብ ኦሞ ዞን ሽግግር ምክር ቤት አስታወቀ

የም/ቤቱ የተለያያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች በዞኑ ኛንጋቶም ወረዳ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ተቋማት የመስክ ምልከታ ያደረጉ ሲሆን መታረም በሚገባቸው ተግባራት ላይ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

በመስክ ምልከታው ጉብኝት ከተደረገባቸው አካባቢዎች የኬንያ አዋሳኝ በሆኑ የኪቢሽ ክላስተር አካባቢዎች የተከናወኑ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው።

በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ዘርፍ በሎኮርለም ቀበሌ በኤል ኤል አር ፒ ፕሮጀክት ግንባታው በመጠናቀቀቅ ላይ የሚገኘውን በጸሐይ ሐይል የሚሰራ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በቋሚ ኮሚቴው ምልከታ የተደረገበት ሲሆን በስኬታማነት ተገምግሟል።

ፕሮጀክቱ በሰከንድ 25 ሜ.ኪ ውሃ የሚያመርት ሲሆን 50 ሺህ ሊትር የሚይዝ የታንከር ግንባታና፣ 2 የከብቶች ውሃ ማጠጫን ጨምሮ 8 ቀበሌያትን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመስመር ዝርጋታ ስራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የወረዳው ውሃ ጽቤት ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ለፌቦ ገልጸዋል።

ም/ቤቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ምልከታ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ በመጥቀስ በኪቢሽ ክላስተር የሎኮርለም ቀበሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ስኬታማ ተግባር የሚያስመሰግን መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ም/ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ታሪኳ ደምሴ ናቸው።

ከወረቀት ሪፖርት ባለፈ በተጨባጭ እየተከናወኑ በሚገኙ የልማት ስራዎች ላይ ወቅታዊ የድጋፍና ክትትል ስራ አጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባው የውሃ ፕሮጀክት ለአካባቢው አርብቶ አደር ማህበረሰብ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ አርብቶ አደሯ ወ/ሮ ኛዋት ኛዌይ ፕሮጀክቱ የዘመናት ችግራቸውን የቀረፈ ከአጎራባች ኬንያ አርብቶ አደሮች ጋር ከሚፈጠር ግጭት የታደጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በ2008 ዓም ግንባታው ተጀምሮ እስካካሁን ያልተጠናቀቀው በኪቢሽ የሎካሙኘን ቀበሌ ጤና ጣቢያ ሌላኛው ምልከታ የተደረገበት ሲሆን አሁንም 90 በመቶ ግንባታው ቢጠናቀቅም ለአገልግሎት ባለመብቃቱ የብልሽት አደጋ የተጋረጠበት መሆኑ በቋሚ ኮሚቴው ተገምግሟል።

ተቋሙ ለአገልግሎት ባለመብቃቱ ከ37 ኪሜ በላይ ተጉዘው ህክምና እንደሚያገኙ የሎካሙኘን ቀበሌ አርብቶ አደሩ አቶ በቃ ወሌ የሚገልጹት።

በክልሉ መንግስት የተጀመረው የጤና ጣቢያ ግንባታ ስራ በራሱ በክልሉ መንግስት መፈታት ያለበት መሆኑን የወረዳው ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ በርቂ አሳስበዋል።

በኬንያ ድንበር አዋሳኝ ላይ የሚገኘው ይኸው ፕሮጀክት የኬንያ ድንበር የተገነባ በመሆኑ የሁለት ሀገር ህዝቦችን የሚያስተሳስር በመሆኑ ፋይደውን ታሳቢ በማድረግ በአፋጣኝ ለማጠናቀቅ መሰራት እንዳለበት የወረዳው ም/ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ኤልያስ አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይም በካንጋቴን አዳሪ ት/ቤት የተማሪ አያያዝን ጨምሮ የካንጋቴን ጤና ጣቢያ ለእናቶች የሚሰጡ ወሊድና ተያያዥ አገልግሎቶች፤ የንብረት አያያዝ ብክነት የታየባቸው ሲሆን የህክምና አገልግሎቱም አፋጣኝ እርምት የሚሻ መሆኑ በም/ቤቱ ተገልጿል።

የመስክ ምልከታው በሌሎች የዞኑ ወረዳዎች አስፈጻሚ ተቋማት ተግባራትን እየፈተሸ የሚገኝ ሲሆን በሌሎች ወረዳዎችም የሚቀጥል መሆኑንም ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።

ዘጋቢ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን