ሀዋሳ፡ ሕዳር 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በከተማው እየተገነባ የሚገኘው የዋና አስፓልት መንገድ የኮሪደር መሰረታዊያን ያሟላ ከመሆኑም በላይ የከተማውን እድገት ይበልጥ ከፍ የሚያደርግ ነው ሲሉ በምስራቅ ጉራጌ ዞን የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዶ አህመድ ገለጹ።
ከአለም ገና-ቡታጅራ የሚገነባውና ቡታጅራ ከተማ ላይ የተጀመረው የአስፓልት ግንባታ እየተፋጠነ ስለመሆኑም ተመላክቷል።
የ14 ቢሊየን ብር በጀት የተያዘለት የአለም ገና-ቡታጅራ ኮንክሪት የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጅማሬውን ቡታጅራ በማድረግ ወደ ተግባር መግባቱ ተጠቁሟል።
ግንባታውን አስመልክቶ ጣቢያችን ያነጋገራቸው የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዶ አህመድ በማህበረሰቡ ዘንድ እስከ ፓርላማ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ የነበረ በመሆኑ÷ መንግስትም ምላሽ የሰጠበት የመንገድ ግንባታ መሆኑና÷ ግንባታው ቡታጅራ መጀመሩ ደግሞ ማህበረሰቡ ለልማት ያለውን ተነሳሽነት ከፍ ያደረገበትና ለግንባታው ምቹ መደላድል የፈጠረበት ነው ብለዋል።
አሁን ላይ በተደራጀ መልኩ ለ24 ሰአት ግንባታ እየተከናወነ በመሆኑ እየተፋጠነ ነው ያሉት ከንቲባው የዋናው የአስፓልት መንገድ ግንባታ አካፋይ ያለውና በአንድ ጊዜ 6 ተሽከርካሪዎችን ማሳለፍ እንዲችል ተደርጎ ጥራት ባለው ሁኔታ እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል።
የ8 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ የዋናው አስፓልት መንገድ ግንባታ የኮሪደር መሰረታዊያን ያሟላ በመሆኑ የከተማውን እድገት ይበልጥ ከፍ የሚያደርግ ስለመሆኑም ከንቲባው ገልጸዋል።
የ17 ኪሎ ሜትር የስማርት ፖል ተከላ የሚካሄድለት የዋናው የአስፓልት መንገድ ግንባታ የከተማ አስተዳደሩን ድምቀት ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።
ያነጋገርናቸው የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት እንዳሉት የዋናው የአስፓልት መንገድ የኮሪደር መሰረታዊያን ባሟላ መልኩ ደረጃውን ጠብቆ በመገንባቱ ደስተኛ ናቸው።
ከተያዘለት ጊዜ አንጻር አሁን ላይ ግንባታው እየተፋጠነ መሆኑን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ ግንባታው ሲጠናቀቅ የከተማውን ደረጃ ከፍ ከማድረግ ባለፈ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
የከተማው ማህበረሰብም ለመንገድ ግንባታው ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለልማት ያለውን ፍላጎት በተግባር አሳይቷል በማለት ይህን ትብብር ቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ዘጋቢ: አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በተከናወነው የተቀናጀ ተግባር የወባ በሽታ ስርጭት እየቀነሰ መምጣቱን በዳዉሮ ዞን የታርጫ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ
ከሪፖርት ባለፈ በተጨባጭ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ላይ ወቅታዊ የድጋፍና ክትትል ስራ አጠናክሮ መቀጠሉን የደቡብ ኦሞ ዞን ሽግግር ምክር ቤት አስታወቀ
የህፃናት የወደፊት የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻልና የተሻለ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመገንባት እየሠራ እንደሚገኝ የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት ገለፀ