በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በ15 መስኮች በተከናወኑ ተግባራት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 01/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በ15 መስኮች በተከናወኑ ተግባራት ከመንግስት ካዝናና ከህብረተሰቡ ሊወጣ የነበረ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን የሳውላ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የከተማ አስተዳደሩ 2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማጠቃለያና የ2018 ዓ.ም የበጋ ወራት በጎ አገልግሎት ተግባር ማስጀመሪያ መድረክ ተካሂዷል።
የሳውላ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ት ቤት ኃላፊ አቶ አንተነህ በለጠ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቱ በራሱ ተነሳሽነት÷ እውቀቱንና ጉልበቱን ተጠቅሞ ማህበረሰቡን የሚያገለግልበት ትልቅ ፋይዳ ያለው ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።
የከተማው አስተዳደር ለሁሉም ቀጠና የሚሆን 70 ቅጠል ቆሮቆሮና 28 ፓኬት ሚስማር በመደገፍና በማስተባበር፣ አመራር በመስጠትና በመከታተል የተሻለ ውጤት እንድናመጣ የበኩላቸውን አስተዋዕጾ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
ባለፈው ክረምት 16 ሺህ 83 ወጣቶችን እና 46 ሺህ 600 የህብረተሰብ ክፍሎችን በ15 የትኩረት መስኮች በማሰማራት ከመንግስት ካዝናና ከህብረተሰቡ ሊወጣ የነበረዉን ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን እንድንችልና ከ46 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
በመድረኩ የተገኙት የሣውላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶ/ር ንጉሴ መኮንን የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት የበጎነትና የመረዳዳት ባህልን ትውልዱ እንዲያዳብር ከማገዝ ባሻገር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራትን ለማከናወን የሚረዳ ዘርፍ ነው ብለዋል።
የከተማው ወጣቶች በክረምት ወራት በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ህብረተሰቡን ለመርዳት ላሳዩት ቁርኝነት አመሥግነው የበጎነት ተግባሩ በበጋውም ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ መሆኑን አንስተዋል ።
ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ም/ ኃላፊ እና ወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምንያህል ባቤና በዘንድሮ የበጋ ወራት የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ዕቅድና በአምናው የክረምት ወራት አፈጻጸም ወቅት የተመዘገቡ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና በተወሰዱ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ የተዘጋጀ ሪፖርት ለተሣታፊዎች አቅርበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ወጣቶች በሰጡት አስተያየት ወጣቱ በራስ ተነሳሽነት ለሚያከናውናቸው የበጎ አገልግሎት ተግባራት ከሚመለከተው የመንግስት አካል ተገቢውን እውቅና ሊያገኝ እንደሚገባው ጠቁመዋል።
የተጀመሩ በጎ አገልግሎት ተግባራት ቀጣይነት እንዲኖራቸውም የመንግሥትና የባለድርሻ አካላትን ድጋፍና ክትትል መጠናከር ይገባዋል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ከተማ ከበደ ወጣቶች ባላቸው እምቅ አቅም በጎ ተግባራትን በማከናወን የህዝባቸውን ተጠቃሚነት ከማጉላት ባሻገር ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ ማድረግና በአከባቢው ገጽታ ላይ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል ።
በመጨረሻም በክረምት ወራት በጎ አገልግሎት የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አካላትና አደረጃጀቶች ዕውቅና ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
ፈጣን ፣ ወቅታዊ እና ተአማኒ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ ዘመኑን የሚመጥን አሰራርን መዘርጋት እንደሚገባ ተገለጸ
በአገሪቱ የተጀመሩ የልማት ጉዞ እንዲሳለጥ የሠላም ዕሴቶችን አጠናክሮ መያዝ እንደሚገባ ተገለጸ
ለሃገራችን ሰላም እና ፀጥታ መስፈን ከሃይማኖት አባቶች የሚጠበቀውን ማናቸውንም አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነን – የሃይማኖት አባቶች