ለሃገራችን ሰላም እና ፀጥታ መስፈን ከሃይማኖት አባቶች የሚጠበቀውን ማናቸውንም አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነን – የሃይማኖት አባቶች

ለሃገራችን ሰላም እና ፀጥታ መስፈን ከሃይማኖት አባቶች የሚጠበቀውን ማናቸውንም አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነን – የሃይማኖት አባቶች

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለሃገራችን ሰላም እና ፀጥታ መስፈን ከሃይማኖት አባቶች የሚጠበቀውን ማናቸውንም አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የተገነባው የነስር መስጂድ እና የመጀመሪያ ዙር የሂፍዝ ተማሪዎች ምረቃ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የመስጅዱ ኢማም ሼህ አደም ሙሐመድ፤ ታሪካዊ መስጅዱን ገንብተው ያጠናቀቁበት እና ለሁለት አመታት ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ተማሪዎችን አስተምረው ለምረቃ ያበቁበት እንዲሁም ኢስላማዊ ኮሌጅና የገበያ ማዕከል የመሰረት ድንጋይ ለማስቀመጥ የበቁበት ቀን መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

መስጅዱ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ዛሬ ላይ ግዙፍ መስጅድ ግንባታ ከማስመረቅ ባለፈ ወደትውልድ ግንባታ ተሸጋግሮ የመጀመሪያ ፍሬዎቹን ለማስመረቅ በቅቷልም ብለዋል።

‎በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አባልና ኡለማ ምክር ቤት አባል ሼህ ኤልያስ አህመድ በበኩላቸው፤ መስጅዱ ለከተማው ውበት የሚያላብስ ለእምነቱ ተከታዮችም ኩራት መሆኑን ተናግረው ቁርዓን መማር የእውቀት የመጀመሪያው ምዕራፍ በመሆኑ ቁርዓንን የሚማር ሁሉ በሚማርበት ጊዜ ዕውቀትን በመቅሰም መልካም ልምድን የሚማርበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመስጅዱ ግንባታ አሻራቸውን ላሳረፉ ሁሉ አላህ በኸይር ይመንዳቸውም ብለዋል፡፡

‎በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙ የእምነቱ ተከታዮች በሰጡት አስተያየትም፤ መስጂዱ ተመርቆ ለዚህ መብቃቱ እንዳስደሰታቸው ገልፀው፤ በቀጣይም ከዚህ የበለጠ ለመስራት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡

‎በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የፌደራልና የክልል መጅሊስ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም መስጅዱ የሚገኝበት የሚዛን አማን ከተማ የመጅሊስ የስራ ሀላፊዎች፤ የመስጅዱን ምርቃት አስመልክተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከመስጂዱ ምረቃ ጎን ለጎን በቀጣይ ለሚያስገነባው ታላቅ ኢስላማዊ ኮሌጅና የገበያ ማዕከል የመሰረተ ድንጋይ በፌዴራል ከፍተኛ የመጅሊስ አመራሮች፣ በፌደራልና በዞን ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች የመሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን ዳጉሳ – ከሚዛን ጣቢያችን