የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል በእናቶችና ህጻናት ብሎም በአዋቂ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ከፍ ባለ ደረጃ ለመስጠት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል በእናቶችና ህጻናት ብሎም በአዋቂ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ከፍ ባለ ደረጃ ለመስጠት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ተገልጋይ እናቶችም በሆስፒታሉ በሰብአዊነት ላይ የተመሰረተና ውጤታማ የሆነ ሁሉን አቀፍ የህክምና አገልግሎት መስጠቱን አድንቀዋል።

የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ቶፊቅ ሞሳ፤ ሆስፒታሉ በህብረተሰቡ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ በ1996 ዓ.ም በውስን የሰው ሃይልና የህክምና ዘርፎች ስራ መጀመሩን አስታውሰው ደረጃ በደረጃ እራሱን በማሳደግ የሚሰጣቸውን የህክምና አገልግሎቶች ከፍ አድርጓል ብለዋል።

ሆስፒታሉ አሁን ላይ የተኝቶ ህክምና አገልግሎት የሚሰጡ አልጋዎች ከ1 መቶ 70 በላይ በማድረስ ከ6 መቶ 50 በላይ የሰው ሃይል ይዞ ውጤታማ የጤና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በተለይም ሆስፒታሉ በሚገኝበት ቀጠና በብዛት የሚከሰቱ ህመሞችን ታሳቢ ያደረጉ የህክምና አገልግሎቶች ለመስጠት ጥናትን መሰረት ያደረገ ስራ ይሰራል ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ በዚህም በእናቶችና ህጻናት ብሎም የአዋቂ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ከፍ ባለ ደረጃ ለመስጠት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህን ማሳካት እንዲቻልም በ2 ሺህ 6 መቶ ካሬ ላይ ያረፈ ህንጻ በመገንባት ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የህክምና ቁሳቁስ ከማስገባት ባለፈ በዘርፎቹ አስፔሻላይዝ ያደረጉ የህክምና ባለሙያዎች መኖራቸው አሁን ላይ በደረጃው ከፍ ያለ የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል ነው ያሉት የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቶፊቅ ሞሳ።

ከጥቂት ወራት በኋላም የድንገተኛ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥበት ህንጻ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል የሚሉት ስራ አስኪያጁ፤ እነዚህ የማስፋፊያ ግንባታዎች ዜጎች ሳይጨናነቁ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችልና የሆስፒታሉን ደረጃም ከፍ የሚያደርግ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በ2017 በጀት አመት ከ5 ሺህ 8 መቶ በላይ እናቶች የእርግዝና እና የወሊድ አገልግሎት ያገኙ ሲሆን ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የድንገተኛ የህክምና አገልግሎት ተሰጥቷል ሲሉም አስረድተዋል።

ሲስተር ሙሉ ሺበሺ በቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል አዋላጅ ነርስ ናቸው።

በሆስፒታሉ ቤተሰባዊ ማንነት ተላብሰው በእንክብካቤ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት በማግኘት ላይ ሳሉ አግኝተን ያነጋገርናቸው እናቶችም በሆስፒታሉ በሰብአዊነት ላይ የተመሰረተና ውጤታማ የሆነ ሁሉን አቀፍ የህክምና አገልግሎት መስጠቱን አድንቀዋል።

በተለያየ ጊዜ በሆስፒታሉ መገልገላቸውን የተናገሩት እናቶቹ ይህን ውጤታማ የሆነው አገልግሎት አሰጣጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን