የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች ላይ እያከናወናቸው የሚገኙ የክትትልና ቁጥጥር ተግባራት የህዝቡ ተጠቃሚነት እንዲሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ገለፀ

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች ላይ እያከናወናቸው የሚገኙ የክትትልና ቁጥጥር ተግባራት የህዝቡ ተጠቃሚነት እንዲሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ገለፀ

ምክር ቤቱ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች አድምጦ መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያደርገው ቁጥጥር አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው በዞኑ የጉመር ወረዳ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በጉራጌ ዞን ምክር ቤት የማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ጥሩነሽ ምኑታ በዞኑ ጉመር ወረዳ አበሱጃ ቀበሌ በተካሄደው የህዝብ መድረክ ላይ እንዳሉት፤ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በማህበራዊ በኢኮኖሚያዊና መልካም አስተዳደር ዘርፎች እያከናወናቸው የሚገኙ የክትትልና ቁጥጥር ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ውጤት እያስገኙ ይገኛሉ።

ምክር ቤቱ ከየሴክተሮች የሚመጡ ሪፖርቶች መርምሮ ግብረ መልስ ከመስጠት ባሻገር ከማህበረሰቡ ጋር የገፅ ለገፅ ውይይት በማድረግ ህዝብ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጀት እየሰራ ይገኛል ብለዋል ወ/ሮ ጥሩነሽ።

በተለይም የህዝብ መድረክ በተካሄደበት የጉመር ወረዳ አበሱጃ ቀበሌ ከህዝቡ የተነሱ የመንገድ የንጹህ መጠጥ ውሃ የመብራትና ሌሎች የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የልማት ጥያቄዎች በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ምላሽ ማግኘት የሚገባቸውን እንዲያገኙ ከአስፈጻሚ አካላት ጋር ከመግባባት መድረሳቸውን ገልጸው፤ የዞን የክልልና የፌዴራል ድጋፍ እና ምላሽ የሚሹት ደግሞ የመከታተል እና የመቆጣጠር ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም በዞኑ ምክር ቤት የማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወ/ሮ ጥሩነሽ ምኑታ ጠቁመዋል።

የጉመር ወረዳ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ትዕዛዙ ጭቅስየ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቶች ከሚያከናውኗቸው ተግባራት አንዱ የክትትልና ቁጥጥር ተግባር ተጠቃሽ እንደሆነ በመግለጽ በየጊዜው መድረክ በመፍጠር ህዝብ የሚያነሳቸው የሰላም የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች በማድመጥ በምላሻቸውም የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲዳብር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

አክለውም ከዚህ ቀደም በወረዳው ህዝብ ሲጠይቃቸው የነበሩ የልማት ጥያቄዎች የየአካባቢው ማህበረሰብ እና የመንግስት አቅም በማስተባበር ምላሽ እንዲያገኙ ተደርጓል ያሉት ዋና አፈ ጉባኤው፤ ተግባሩ አጠናክሮ በማስቀጠል ቀሪ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙና ተጠቃሚነቱ እንዲጎለብት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የአበሱጃ ቀበሌ በግብርናው ዘርፍ ትርፍ ከሚያመርቱ የወረዳው ሞዴል ቀበሌዎች አንዱ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ትዕዛዙ፤ በቀበሌው አርሶ አደሩ ምርቱን ገበያ አጓጉዞ በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ የሚያስችለው መንገድ ለመገንባት በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

አቶ ቶፊቅ በሽር ኤልያስ መሐመድ እና ወ/ሮ ባሮ መሀመድ በጉመር ወረዳ የአበሱጃ ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው።

በህዝብ መድረኩ ላይ በሰጡት አስተያየት የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት በየአካባቢው ህዝብ የሚያነሳቸው የሰላም፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አድምጠው መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያደርጉት የክትትልና ቁጥጥር ተግባራት አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በአካባቢያቸው መንግስት ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ በተለይም የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታን ጨምሮ የመብራትና የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

አክለውም መንግስት ከቀበሌው ማህበረሰብ የሚፈልጋቸው ድጋፎች ሁሉ ማህበረሰቡን ለማገዝ ዝግጁ ስለመሆኑም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን