የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት የተጀመረው ቅንጅታዊ ርብርብ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል -የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ
ሀዋሳ፣ ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት የተጀመረው ቅንጅታዊ ርብርብ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስገነዘበ፡፡
ክልላዊ ወቅታዊ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት ያለመ የንቅናቄ መድረክ በጂንካ ከተማ ተካሂዷል።
ከወትሮው በተለየ መልኩ የተከሰተው ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት በሁሉም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መንስኤ ስለመሆኑ ወቅታዊ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህንን ተከትሎም ነው በክልሉ ወቅታዊ የወባ በሽታ ስርጭትን የመከላከልና የመቆጣጠር የንቅናቄ መድረክ የተሰናዳው።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ እና የጤና ፕሮግራሞችና የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍ ሀላፊ አቶ መና መኩሪያ በአለማችን የወባ በሽታ ስርጭት ጫና ካለባቸው 18 ሀገራት መካከል ሀገራችን ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ጠቅሰው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም በበሽታው ስርጭት የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን እያስተናገደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የእድገት ማነቆ የሆነውን የወባ ወረርሽኝ በመከላከል ረገድ ላለፉት አስርት ዓመታት ፈርጀ ብዙ ስራዎች መከናወናቸውን ያነሱት ኃላፊው እንደ ሀገር ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ተነድፎ ሲተገበር በመቆዬቱ መሻሻሎች መታዬታቸውን ጠቅሰዋል።
ይሁንና ግን ባለፉት 2 ዓመታት ከወትሮው በተለዬ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች የተከሰተው ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት ስጋት የፈጠረ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ለአብነትም በ2018 ዓ.ም ከ700 ሺህ በላይ ዜጎች ላይ በተደረገ የወባ ምርመራ ከ 40 በመቶ በላይ ዜጎች የሽታው ተጠቂ ሆነው መገኘታቸውን በማሳያነት አቅርበዋል።
አሁንም ቢሆን የአየር ሁኔታው ለበሽታው ስርጭትት ምቹ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑንም ነው ኃላፊው የገለጹት።
የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል በክልሉ የተከናወኑ ተግባራት በዝርዝር ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በቀጣይ የዘርፉ ተግባራት በቅንጅት መከናወን እንዳለባቸው ተመላክቷል።
ከንቅናቄው ተሳታፊዎች መካከልም የአሪ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ በድሉ ባጊማስ እና የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ተወካዩ አቶ አንዳርጌ ቶቤ በዞኖቹ የበሽታው ስርጭት በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ጉዳት ማስከተሉን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት መጠነኛ መሻሻሎች ቢኖሩም የአየር ሁኔታው ለበሽታው ስርጭት ምቹ ሆኖ በመቀጠሉ በንቅናቄ የተወጠኑ ተግባራትን በትኩረት ማከናወን እንደሚገባም ነው የገለጹት።
የክልሉ ጤና ቢሮ ከማላሪያ ኮንሰርተም ጋር በመተባበር ባሰናዳው የንቅናቄ መድረክ የጤናው ዘርፍ ባለ ድርሻ አካላትን ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊዎችም ተሳታፊዎች ሆነዋል።
ዘጋቢ:- ወንድሜነህ አድማሱ ከጂንካ ቅርንጫፍ ጣቢያ

More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 27/2018 ዓ.ም #ደሬቴድ – ቀጥታ ስርጭት #ዜና24 #ዜና #ደቡብቴቪ
የልማት ሥራዎችን ለማሣካት የሚመደብ በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ ተመላከተ
ሴቶች የቁጠባን ባህል በማዳበር የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ በትጋት ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለጸ